ሀገር አቀፍ የማረሚያ ቤት አስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጥ ወጥነት ሁኔታን አስመልክቶ በተደረገ ጥናት ላይ የፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታን ጨምሮ የፌዴራልና የክልል ማረሚያ ቤት ኮሚሽነሮችና ምክትል ኮሚሽነሮች እንዲሁም ጉዳዩ የሚመለከታቸዉ ባለሙዎች በተገኙበት የግብአት ማሰባሰቢያ ዉይይት ተካሂዷል።
በዚህ ወቅት ጥናቱ በአጠቃላይ ከፌዴራል እስከ ክልል ብሎም ከክልል ክልል ያለዉ የማረምና የማነፅ ስራ ወጥነት የጎደለዉ መሆኑን መነሻ በማድረግ አገልግሎት አሰጣጡን በተቀራረበና ወጥነት ባለዉ መንገድ በምን መልኩ እናድርስ ለሚለዉ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ጥናቱ መካሄዱ ተገልጿል።
የማረሚያ ቤት አገልግሎት አሰጣጥን የተሻለና ወጥነት ያለዉ ለማድረግ ባለፉት የለዉጥ አመታት በርካታ ስራዎች መሰራታቸዉንና የተሻለ ሪፎርም በመደረጉም የማረምና የማነፅ ስራዉ የተሻለ ለዉጥ ማምጣቱ የተገለፀ ሲሆን ፤ ሆኖም ግን በመሰረታዊነት መለወጥ ያለባቸዉ ቀሪ ተግባራት መኖራቸዉ ተመላክቷል፡፡
ይህንኑ ተግባር በትኩረት ለመተግበር ያስችል ዘንድም የፍትሕ ሚኒስቴር ባዘጋጀዉ የአምስት አመት ስትራቴጂክ እቅድ ዉስጥ አንደኛዉ አምድ የማረምና የማነፅ ስራዉን ማስተካከልና ማዘመን መሆኑንና ለዚህ ተግባር መሳካት የፍትህ ስርአቱ በጋራ ሊሰራበት እንደሚገባ ተገልጿል።
በተጨማሪም ተቋሙ ወደ ማረሚያ ቤት የሚሄደዉን ቁጥር ለመቀነስ የሚያስችል አማራጭ የቅጣት ማስፈፀሚ ረቂቅ አዋጅ፣የመልሶ መቀላቀልና ነጻ የህግ ድጋፍ አገልግሎት ረቂቅ አዋጆች ማዘጋጀቱንና አዋጆቹ ፀድቀዉ ወደ ተግባር ሲገቡ ስራዉን የበለጠ እንደሚያግዙ ተመላክቷል።
የማረምና ማነፅ ስራዉን አስመልክቶ ከፌዴራል ጀምሮ በክልሎች ደረጃ የሚሰጡ ስልጠናዎች፤ የምገባ ስርአት፤ የትጥቅ ስርአትና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ወጥ እንዲሆኑ በማድረግ ማረሚያ ቤት የራሱ የሆነ ቀለም እንዲይዝ ማድረግና በክልል ደረጃም ነባራዊ ሁኔታን ባገናዘበ መልኩ የተሻለና የተቀራረበ አገልግሎት ሊሰጡ እንደሚገባም ተገልጿል።
ጥናቱ የማረሚያ ቤት አገልግሎት አሰጣጥ፤ተቋማዊ አደረጃጀትና አስተዳደር፤ጥበቃና ደህንነት ላይ ዳሰሳ በማድረግ ለተለዩ ችግሮች የመፍትሄ ሀሳብ ማመላከትን ዓላማዉ አድርጎ የተሰራ ሲሆን፤ የጥናቱ ግብም ማህበረሰቡ ሰላማዊና የተረጋጋ ኑሮ እንዲኖር ማስቻል ብሎም ታራሚዎች መልካም ባህሪ አምጥተዉ ጥሩና አምራች ዜጋ እንዲሆኑ ማስቻል መሆኑ ተገልጿል።
የዉይይቱ ተሳታፊዎች ጥናቱ ማረሚያ ቤቶች ያሉበትን አሁናዊ ሁኔታ በሚገባ የዳሰሰና ያመላከተ መሆኑን ጠቅሰዉ በተለይም የወጥነት ችግሮቹ ከክልል ክልል በዘለለ በአንድ ክልል ዉስጥ ያሉ ዞኖችና ወረዳዎች ጭምር የሚስተዋል ችግር መሆኑን አንስተዋል፤በተጨማሪም በጥናቱ መካተት እና ግልፅ ሊሆኑ የሚገባቸዉንጉዳዮችን በተመለከተ ጥያቄዎች አንስተዉ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
ጥናቱን የፌዴራል ማረሚያ ቤት፣ሴንተር ፎር ጀስቲስ እና የፍትህ ሚኒስቴር በጋራ በመሆን ያጠኑት መሆኑ የተገለፀ ሲሆን ሴንተር ፎር ጀስቲስ ጥናቱ ሲካሄድ ጀምሮ እስካሁን እያደረገ ላለዉ ድጋፍ ምሰጋና ተችሮታል፡፡