በተራሚዎች መልሶ መቀላቀል ረቂቅ አዋጅ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተካሄደ

Draft Proclamation on Prisoner Reintegration Discussed with Stakeholders

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ከፍትሕ ለሁሉም ፕሪዝን ፌሎሺፕ (Justice For All-PFE) ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር በተራሚዎች መልሶ መቀላቀል ረቂቅ አዋጅ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር የውይይት መድረክ አካሂዷዋል፡፡

የፍትሕ ሚኒስቴር የሕግና ፍትሕ አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ በላይሁን ይርጋ በውውይት መድረኩ እንዳሉት በሀራችን ለመልሶ መቀላቀል በቂ ትኩረት ተሰጥቶ፣ የሕግ ማዕቀፍ ተዘጋጅቶ፣ የመልሶ መቀላቀል ተግባርን የሚያከናውን አካል በግልፅ ተለይቶ እና የማስፈፀሚያ ስልቶች ተዘጋጅተው ተግባራዊ ባለመሆናቸው በጉዳዩ ላይ በተለያዩ ጊዜያት ብዙ ስራዎች ቢሰሩም ስኬታማ ሳይሆኑ መቅረታቸውን ተናግረዋል፡፡

አክለውም መልሶ መቀላቀል በግልፅ የተዘረጋ ስርዓት እንደሚፈልግ ጠቅሰው ነገርግን ይህ እስኪሆን መጠበቅ ትተን ያሉንን የአሠራር ስርዓቶች አጠናክረን ስራዎችን በመጀመርና በጉዳዩ ላይ ርብርብ በማድረግ መሠረታዊ የሆነ ለውጥ ማምጣት እንችላለን ሲሉ ገልፀዋል፡፡

የፍትሕ ለሁሉም ፕሬዝደንት ፓስተር ዳንኤል ገ/ስላሴ በበኩላቸው ተቋማቸው ከፍትሕ አካላት ጋር ላለፉት ሶስት አስርት አመታት በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ሲሰራ እንደቆየ አውስተው፤ በመልሶ መቀላቀል ጉዳይ ላይ ለረዥም ጊዜ ከሚመለከታቸው የፍትሕ አካላት ጋር ሲወያይበት እንዲሁም ጥናት ሲያካሂድበትና የተለያዩ ሀገራትን ልምድ ምልከታ ሲያደርግ የቆየበት ጉዳይ መሆኑን ጠቁመው፣ ዛሬ በዚህ ደረጃ ረቂቅ ሕግ ሆኖ ለውይይት መቅረቡ ትልቅ ተግባር መሆኑን በመጥቀስ ፍትሕ ሚኒስቴርን አመስግነዋል፡፡

በመድረኩ በረቂቅ አዋጁ ላይ ገለፃ የተደረገ ሲሆን፣ በተለይም የወንጀል ደጋጋሚነትን መቀነስ የሚያስችል ሥርአት ለመዘርጋት ፣ በዚህም የሕዝብ ሰላም፣ ደኅንነትና ፀጥታን ለመጠበቅ፤ ታራሚዎች እውቀትና ክህሎት አግኝተው እንዲወጡ ለማስቻል፤ ጠንካራና ቅንጅታዊ አሠራር እና የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ለማድረግ ረቂቅ አዋጁ አሰፈላጊ እንደሆነ ተመላክቷል፡፡

ረቂቅ አዋጁ በዋናነት ታራሚዎች ከማረሚያ ቤት ቆይታቸው በኋላ ወደ ማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉና ድጋፍ እንዲያገኙ የሚያደርጉ፣እርምጃዎቹ ታራሚው በማረሚያ ቤት እያለ እና ከወጣ በኋላ የሚተገበሩ እንደሆነ፤ ታራሚዎች ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ስነ-ልቦናዊ ድጋፎችን ጨምሮ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን ያጠቃለለ እና ተግባሩ የብዙ ባለድርሻ አካላት ተሳትፎን የሚጠይቅ ሂደትን የተከተለ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

በመጨረሻም በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ከተሳታፊዎች ጋር ሰፋ ያለ ውይይት የተደረገ ሲሆን፣ ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች በስራ ሀላፊዎች እና በአርቃቂ ቡድኑ ምላሽ ተሰጥቶባቻው የውይይት መድረኩ ተጠናቋል፡፡

በመድረኩ ከፍትሕ ሚኒስቴር፤ ከሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር፣ ከጤና እና ከስራና ክህሎት ሚኒስቴር የተወጣጡ የስራ ሀላፊዎች እና ባለሙያዎች ፤ ከፌደራል እና ከክልል ፖሊስ እንዲሁም የማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን እና ከክልል ፍትሕ ቢሮዎች የተወጣጡ የስራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

የቅርብ ጊዜ ዜናዎች