የአሜሪካን ኤምባሲ በፍትሕ ሚኒስቴር ስር የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ትግበራ ምዕራፍን በጊዜያዊነት ለሚያስተባብረው የሽግግር ፍትሕ ተቋማት ግንጅታዊ መድረክ ሴክሬታሪያት ድጋፍ የሚሆኑ የተለያዩ ቁሳቁሶችን አበርክቷል፡፡
ኤምባሲውን በመወከል ድጋፉን ያበረከቱት በአሜሪካን ኤምባሲ የአይ. ኤን. ኤል የኢትዮጵያ ዳይሬክተር የሆኑት የለና ዘሩ እና ፕሮግራም አስተባባሪው ሚስተር ጆሴፕ ጊፕሰን ሲሆኑ ፍትሕ ሚኒስቴርን በመወከል ድጋፉን የተረከቡት የፍትሕ ሚኒስቴር የመንገስት ሕግና ፍትሕ አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ በላይሁን ይርጋ ናቸው፡፡
በድጋፍ ከተበረከቱት ቁሳቁሶች መካከል ኮምፕዩተሮች፣ ፕሪንተሮች፣ ፕሮጀክተሮች፣ የፎቶ ካሜራ ፣የመቅርፀ ድምጽ መሳሪያዎች፣ ሀርድ ዲስኮች እና ለቢሮ አገልግሎት የሚውሉ የፈርኒቸር ውጤቶች ይገኙበታል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ በላይሁን ይርጋ ድጋፉን ከተረከቡ በኋላ ባስተላለፉት መልዕክት የአሜሪካን ኤምባሲ በተለያዩ የሕግ እና ፍትሕ ጉዳዮች ዙሪያ በዩኤስ አይድ ፍትሕ አክቲቪቲ እና መሰል ፕሮግራሞች አማካኝነት ከፍትሕ ሚኒስቴር ጋር አብሮ በመሥራት ላበረከተው ሚና አመስግነው የተበረከተው ድጋፍም በሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ትግበራ ምዕራፉ ውጤታማነት የራሱን ሚና እንደሚያበርክት ገልጸዋል፡፡ የሽግግር ፍትሕ ትግበራው የሁሉንም ትብብር የሚፈልግ መሆኑን የገለጹት ክቡር ሚኒስቴር ዴኤታው ኤምባሲው የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲውን ተፈጻሚነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተስፋ እንደሚያደርጉም ገልጸዋል፡፡