በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ዐቃቤ ሕግ ዳይሬክቶሬት ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሄደ

Public Prosecutor's Directorate for Crimes Against Women and Children Holds Discussion with Stakeholders

በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ዐቃቤ ሕግ ዳይሬክቶሬት ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና ተቋማት ከተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ጋር የ2016 በጀት ዓመቱን የ6 ወር ሪፖርት አቅርቦ ውይይት አካሄደ፡፡ በውይይቱም የህብረተሰቡ ተሳትፎ በፍትሕ ስርዓት ያለውን ሚና አስመልክቶ መነሻ ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡

በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ዐቃቤ ሕግ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሪት ጽጌ የማነ በበጀት ዓመቱ ባለፉት 6 ወራት ታቅደው የተከናወኑ ተግባራትን በአዲስ አበባ ከተማ በ11ዱም ክፍለ ከተሞች ከሚገኙ የትምህርት ጽ/ቤት፣ የጤና ጽ/ቤት፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ፖሊስ፣ የነዋሪው ማህበር፣ የእድሮች ማህበር፣ የሴቶች ማህበር፣ የወጣት ማህበር፣ የስርዓተ ጾታ ባለሙያዎች፣ ሰላምና ፀጥታን የያዘ የሴቶችና ሕፃናት ጥቃት ተከላካይ ኮሚቴ አባላት እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ሪፖርታቸውን ሲያቀርቡ ከሴቶችና ሕፃናት ግድያ ጋር በተያያዘ በተለያየ የአገዳደል ደረጃ በደል በማድረስ ህይወታቸው እንዲያልፍ በማድረግ ግድያዎች ተፈፅመው ክስ ከተመሰረተባቸው መዛግብት ውስጥ በርካታ መዛግብት ላይ በዐቃቤ ሕግ ውሳኔ ያገኙ ሲሆን የተቀሩት መዛግብቶች ደግሞ በምርመራ ላይ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

ዳይሬክተሯ ባቀረቡት ሪፖርት ባለፉት ስድስት ወራት በአስገድዶ መድፈር፣ በአካል ላይ የሚደርስ ጉዳት እና በሕፃናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ጋር ተያይዞ በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ በሁሉም ክፍለ ከተሞች እና ድሬዳዋ ከተማን ጨምሮ በርካታ መዛግብት የቀረበ ሲሆን ከቀረቡት መዛግብት ውስጥም ብዙዎች በዐቃቤ ሕግ ውሳኔ አግኝተዋል የተቀሩት በፖሊስ የምርመራ መዝገብ ላይ ይገኛሉ ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ዳይሬክተሯ በሪፖርታቸው ላይ አያይዘውም በአዲስ አበባ ከተማና በድሬዳዋ ከተማ በሚገኘው የተቀናጀ የፍትሕ እንክብካቤ ማዕከል የህክምና ተቋም ላይ የአስገድዶ መድፈር፣ የግብረ-ሰዶም ጥቃት፣ የግብረ-ስጋ ድፍረት በደል ጉዳት ደርሶብኛል በማለት ባለፉት 6 ወራት 1036 ተጎጂዎች መጥተው የስነ-ልቦና ምክርና የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ተደርገዋል ከእነዚህ ተጎጂዎች መካከልም በአብዛኛው ጥቃት እየተፈፀመባቸው ያለው በአስገድዶ መድፈር ወንጀል ሆኖ ሕፃናትን ጨምሮ 18 ዓመት ያልሞላቸው ሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ናቸው በማለት ያብራሩ ሲሆን ጥቃት ከሚፈፀምባቸውም ቀዳሚውን ስፍራ የያዙት ለሚኩራ፣ የካ፣ አቃቂ ቃሊቲና ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተሞች ላይ በአብዛኛው የተፈፀመ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡

በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ዐቃቤ ሕግ ዳይሬክቶሬት የቡድን አስተባባሪ የሆኑት አቶ ቶላ ጃራ በውይይት መድረኩ ላይ የህብረተሰብ ተሳትፎ በፍትሕ ስርዓት ያለውን ሚና አስመልክቶ መነሻ ጽሁፍ ሲያቀርቡ እንደገለፁት የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ እና ፍትሕ የማስፈን ኃላፊነት የመንግሥት ግዴታ መሆኑን እሙን ቢሆንም ያለህብረተሰብ ተሳትፎ ፍትሕን ማረጋገጥ ስለማይቻል ህብረተሰቡ በፍትሕ ስርዓቱ ላይ ያለው ሚና ወሳኝ እና ቁልፍ ነው ብለዋል፡፡

አቶ ቶላ አክለውም ህብረተሰቡን ያላካተተና ያልተሳተፈበት ፍትሕ ውጤት ስለማያመጣና ሊረጋገጥ ስለማይችል ፍትሕ እንዲኖር የማድረግ ጉዳይ በህብረተሰቡ እጅ ላይ በመሆኑ ህብረተሰቡ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ጥፋተኛና ወንጀለኛ እንዲቀጣ በምናደርገው ሂደት ከጎናችን በመቆም በትብብር እንስራ ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በውይይቱ ላይ ተሳታፊዎች በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከል የሐይማኖት አባቶች ድርሻቸውን ቢወጡ፣ በትምህርት ቤት እና በሌሎች ተቋማት ላይ መሰራት ቢችል፣ ከፍትሕ አካላት ጋር ተቀናጅተን ከጥቃት ተከላካይ ኮሚቴ ጋር በጋራ አቅደን ብንሰራ የሚሉና ሌሎች ጥያቄዎችንና አስተያየቶችን ያነሱ ሲሆን በተነሱት ላይም ዳይሬክተሯ ማብራሪያና ምላሽ በመስጠት አብዛኞቹ ሕፃናት እየተጠቁ ያሉት በቤተሰብ ስለሆነ ማስቀረት ባንችል እንኳን መቀነስ ስለምንችል ይሄንን ለማድረግ የበኩላችንን እንወጣ ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

Tagged Under: 2016 budget year • abuse • addis ababa • against • assault • child • Child Abuse • Child Protection • children • community participation • Crimes • Crimes Against Children • Crimes Against Women • Dire Dawa • domestic • Domestic Violence • Gender-Based Violence • Justice System • Legal Proceedings • Prosecutors • public • Rape • sexual • sexual assault • six-month report • Stakeholder Engagement • violence • women
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች