የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የተቋም ግንባታ እና ሪፎርም ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ኤርሚያስ የማነብርሀን የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የ3 ዓመት የፍትሕ ዘርፍ የትራንስፎርሜሽን እቅድ ፍኖተ ካርታን የ2017 በጀት ዓመት የ 6ወራት አፈፃፀምን ከልዑክ ቡድናቸው ጋር በሰመራ ከተማ በመገኘት ገምግመዋል።
ክቡር ሚኒስትር ዴኤታ የሱፐርቪዥኑን ዓላማ በተመለከተ እንደገለፁት የአፋር ክልል በ2017 በጀት ዓመት ባለፉት 6 ወራት ከ3 ዓመት የፍትሕ ዘርፍ የትራንስፎርሜሽን እቅድ ፍኖተ ካርታ አንፃር ያከናወናቸውን ተግባራት ለመገምገምና የፍትሕ ስርዓቱን ለማሻሻል በሚደረገው ጥረት የታዩ ክፍተቶችን በመለየት አስፈላጊውን ድጋፍና እገዛ ለማድረግ ያለመ መሆኑን ነው፡፡
የክልሉ የፍትሕ ቢሮ ኃላፊ ክቡር አቶ ኡስማኤል መሀመድ በበኩላቸው የፍትሕ ሚኒስቴር ልዑክ ቡድን የክልሉን የትራንስፎርሜሽን እቅድ የ6 ወራት አፈፃፀም ለመገምገም በመምጣቱ አመስግነው፣ የትራንስፎርሜሽን እቅድ በአፋር ክልል ባለፉት ወራቶች የተከናወኑ ተግባራቶችን ከ 10ሩ መሠረታዊ አምዶች አንጻርና በመፈፀም ረገድ የታዩ ክፍቶችን አቅረበው ክፍተቶችን በመለየት የመፍትሔ እርምጃዎችን ክልሉ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት እየወሰደ መሆኑን ገለፃዋል።
ሃላፊው እንደገለፁት ከመሰረተ ማኅበረሰብ ፍትሕ አገልግሎት አንፃር በክልሉ ያሉ ማህበረሰቡ የሚጠቀሙባቸውን ባህላዊ የግጭት መፍቻ ስርዓቶች እንደ መድ’ዓ ያሉ የዳኝነት ስርዓቶችን ወደ ጽሑፍ በመቀየር (Codify) በማድረግ ለትውልድ እንዲተላለፍና ባህላዊ የፍትሕ ስርዓቱ እንዲጠበቅ የማድረግ ስራዎች መሰረታቸው እንዲሁም ለባህላዊ የዳኝነት ስርዓት እውቅና መስጫ የሕግ ረቂቅ አዘጋጅተው ለባለድርሻ አካላት ውይይት ዝግጁ ማድረጋቸውን፣ በአይሳዒታ ከተማ ማኅበራዊ ፍትሕ ማዕከል መክፈተቻውን ጠቁመዋል።
አክለውም ከፍትሀ ብሔር ፍትሕ አስተዳደር አንጻር የቤተሰብ ህጉን ረቂቅ አዘጋጅተው ከባለድርሻ አካላት ግብዓት እየተሰበሰበ መሆኑን፣ ከወንጀል ፍትሕ አስተዳደር አንጸር በክልሉ የተበራከቱ የወንጀል አይነቶችን በተለይ ከኢኮኖሚያዊና የኮትሮባንድ ወንጀሎችን እንዲሁም ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን በጥናት በመለየት ወንጀልን የመከላከል ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ፣ የታራሚዎችን መሠረታዊ የዕለት ፍጆታ ከ 24 ብር ወደ 100 ብር ማሳደጋቸውንና ከአስተዳደር ፍትሕ አንጻር የቅሬታ ሰሚና መልካም አስተዳደር ኮሚሽን ማቋቋማቸውን የቅሬታ አቀራረብ ስርኣት ድጋፍና ክትትል ረቂቅ ደንብ፣ የሲቪክ ማህበራትና የጠበቆች ማህበራት ረቂቅ አዋጅ አዘጋጅተው ለማፅደቅ በሂደት ላይ መሆናቸውን አውስተዋል።
በተያያዘም ቢሮው የክልሉን ማኅበረሰብ የሕግ ንቃተ ህሊና ለማሳደግ በርካታ የንቃተ ሕግ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ እንዲሁም በክልሉ ያሉ የፍትሕ ቢሮዎችን በቴክኖሎጂ ግብዓቶች ከአጋር አካላት በተገኘ ድጋፍ ማሟላት መቻሉን፣ ቅንጅታዊ አሠራርና ለማጠናከር እንዲሁ በክልሉ ከሚገኙ የፍትሕ አካላት ጋር በርካታ ስራዎች መስራታቸውን የገለፁት የቢሮው ሃለፊ፣ የትራንሽፎርሜሽን እቅዱ ላይ የተቀመጡ የተወሰኑ አምዶችን ለመተግበር የበጀትና የቴክኖሎጂ ግብዓት ችግር መኖሩን እንደ ክፍተት አንስተዋል። በቀጣይም የታዩ ክፍተቶችን በማረም በእቅዱ የተቀመጡ ግቦችን ገቢራዊ በማድረግ የክልሉን ሕዝብ የፍትሕ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠትና የተገልጋይ እርካታን ለማሳደግ እንደሚተጉ ገልፀዋል።
የፍትሕ ሚኒስቴር የትራንስፎርሜሽን እቅድ አስፈፃሚ ግብረ-ኃይል የክልሉን የትራንስፎርሜሽን እቅድ፣ የ6 ወር የጽሑፍና የገለፃ ሪፖርት መነሻ በማድረግ ላነሳቸው ጥያቄዎች የክልሉ አመራሮች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በመጨረሻም ክቡር ሚኒስቴር ዴኤታ በክልልሉ በ ፍትሕ ዘርፍ የተሰሩ ስራዎች መልካም መሆናቸውን አንስተው፣ በቀጣይም የክልሉን ህበረተሰብ የፍትሕ ጥያቄዎችን ለመፍታትና የህብረተሰብ እርካታን ለማሳደግ የፍትሕ አገልግሎቶች በቴክኖሎጂ መደገፍ እንደሚገባቸው፣ የአስተዳደር ሥነ ሥርዓት ህጉ ላይ ለአስፈጻሚው አካላት ሥልጠናዎችን መስጠትና አተገባበሩን መከታተል፣ ንቃተ ሕግን የመገናኛ ብዙሀን አማራጮችን በመጠቀም ማሳደግ እንደሚገባ እንዲሁም ያልጸደቁ ህጎችን የመሰረተ ማኅበረሰብ ፍትሕና የቤተሰብ ህጉና ሌሎች ጸድቀው ወደ ትግበራ ምዕራፍ እንዲሻገሩ ጥረት ማድረግ እንደሚገባ በተለይም መተግበር ያልተጀመሩ አምዶችን ትኩረት ተሰጥተዋቸው እንዲሰሩ አሳስበዋል።
የፍትሕ ሚኒስቴርም የአፋር ክልል በተለይ የፍትሕ ቢሮ የትራንስፎርሜሽን እቅዱን ለመተግበር ለሚያደርገው ጥረት እንደሁልጊዜ አስፈላጊውብ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ክቡር ሚኒስቴር ዴኤታው ገልፀው በክልሉ ለመስክ ምልከታ በነበራቸው ቆይታ ለተደረገላቸው አቀባበል ምስጋና አቅርበዋል።
በግምገማ መድረኩ የአፋር ክልል ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ፍትሕ ቢሮ ኃላፊ ክቡር አቶ ኢስማኤል መሀመድና ሌሎች የቢሮው መካከለኛ አመራሮች፣ የክልሉ ፖሊስ ኮምሽን ምክትል ኮምሽነር፣ የክልሉ የትራንስፎርሜሽን እቅድ አስፈፃሚ ፎካል ፐርሰንና የማረሚያ ቤት ኃላፊዎች ተገኝተዋል።