የፍትህ ሚንስቴር እና ተጠሪ ተቋማቱ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ሃብታቸውን አስመዘገቡ

Ministry of Justice and Partner Organizations Register High-Level Officials' Assets

የፍትሕ ሚንስቴር እና የተጠሪ ተቋማቱ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ሃብታቸውን እና የገቢ ምንጫቸውን ኮሚሽኑ ባለማው አዲስ ሶፍት-ዌር የማስመዝገብ ስነ-ስርዓት በፍትሕ ሚንስቴር መሰብሰቢያ አዳራሽ አካሄደዋል፡፡

የሃብት ማስመዝገብ ስነ-ስርዓቱን አስመልክቶ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የፌዴራል ስነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ወዶ አጦ እንደገለጹት ሙስና ለአገራችን ሰላምና እድገት ጠንቅነቱ ከእለት ወደ እለት እየጨመረ መምጣቱን ገልጸው ዜጎች ሰርተው የሚለወጡባት፣ ማኅበራዊ ፍትሕ የሚገኝባት አገር ለመገንባት ኮሚሽኑ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ስለሆነም የአገራችንን ደሀ ሕዝብ ከብዝበዛና እንግልት ለመጠበቅ በመንግስታዊ አገልግሎት ውስጥ ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለበት አሠራር ለመዘርጋት የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ የቆዩ መሆኑን የገለጹት ም/ኮሚሽነሩ እስካሁን የሀብት ማስመዝገብ ስራ በማንዋል ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰው በወረቀት ሲሰራ የነበረው የሀብት ምዝገባ ስርዓት ከተደራሽነት፣ ከወጪ ብክነት እና መሰል ችግሮች አንጻር የራሱ ውስንነቶች እንደነበሩበት አብራርተው በወረቀት ላይ ሲደረግ የነበረውን አሠራር ወደ ኤሌክትሮኒክስ እንዲሸጋገር መደረጉ በአገር ደረጃ ለሚደረገው የጸረ ሙስና ትግል የጎላ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡

በመቀጠልም የፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ ባስተላለፉት መልክት የተቋሙ አመራሮች፣ የተጠሪ ተቋማት አመራሮች እንዲሁም የተቋሙ ሰራተኞች ኃብታቸውን በዲጂታሉ አሠራር ባግባቡ እንዲያስመዘግቡ አሳስበው ተቋሙ ካለው ኃላፊነትና ተግባር አንጻር ለሌሎች ዓርአያ ሆኖ መገኘት ይገባዋል ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል ኃብት የማስመዝገብ ግዴታቸውን የማይወጡ፤ ሀብታቸውን ያላስመዘገቡ ትክክለኛ ያልሆነ መረጃ የሚሞሉ፣ እንዲሁም ምንጩ ያልታወቀና ጥርጣሬ የሚፈጥር መረጃ ተሞልቶ ሲገኝ ተቋሙ ተገቢውን የማጣራት ስራ በመሥራት እርምጃ እንደሚወስድም በአጽኖት ገልጸዋል፡፡

ቀጥለውም የፌዴራል ስነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን ዓላማውን ሙሉ ለሙሉ ለማሳካት፣ ለማጣራት እና የመረጃ ጥራትን በጠበቀ መልኩ ለመሥራት ያመች ዘንድ አሰራሩን በዘመናዊ መልክ መቀየር በመቻላቸው ምስጋና አቅርበዋል፡፡በመጨረሻም ሚኒስትሩ በበየነ መረብ ስርዓት ታግዞ በሚካሄደው የሀብት ምዝገባ ስርዓት አማካኝነት የራሳቸውን ኃብት ያስመዘገቡ ሲሆን ሌሎች የተቋሙ ከፍተኛ አመራሮችና የተጠሪ ተቋማቱ አመራሮችም ኃብታቸውን አስመዝግበዋል፡፡ በቀጣይም የተቋሙ እና የተጠሪ ተቋሟት መካከለኛ አመራሮች እና ባለሙያዎች ሀብታቸውን እንደሚያስመዘግቡ ይጠበቃል፡፡

Tagged Under: Asset Registration
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች