የኢፌዴሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሃና አርዓያስላሴ እና የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምሕረት በጋራ በመሩት እና ትኩረቱን የሽግግር ፍትሕ ላይ ባደረገው በዚህ ውይይት ላይ ከፍትሕ ሚኒስቴር እንዲሁም ከፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተውጣጡ የስራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል፡፡
የውይይቱ ዓላማ ተቋማቱ የሽግግር ፍትሕ ትግበራ ምዕራፍ ውስጥ ተቋማዊ ነጻነታቸውን ጠብቀው ለሂደቱ መሳካት የበኩላቸውን ሚና ስለሚወጡበት ሁኔታ የጋራ ምክክር ማድረግ ነው ሲሉ ንግግራቸውን የጀመሩት የፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሃና አርአያስላሴ መድረኩ በተለይም በሕግ ዝግጅት ሂደት የሁለቱ ተቋማት ተናቦ እና ተቀናጅቶ መሥራት በትግበራ ሂደት ሊፈጠሩ የሚችሉ ተግዳሮቶች ከስር ከስር እየፈቱ ለመሄድ ሁነኛ አበርክቶ አለው ብለዋል፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምሕረት በበኩላቸው በሽግግር ፍትሕ ትግበራ ምዕራፍ ውስጥ የሽግግር ፍትሕ ጉዳዮችን የሚመለከተውን ልዩ ችሎት በማቋቋም ረገድ ትልቁን ሚና የሚጫወቱት የፌዴራል ፍርድ ቤቶቹ እንደመሆናቸው መጠን ግልጽነት የሰፈነበት እና ጠንካራ ቅንጅታዊ አሠራር ለመፍጠር ወቅቱን የጠበቀ ምክክር ማድረጉ ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል፡፡
በውይይት መድረኩ የሽግግር ፍትሕ እንዲተገበት ከተወሰነበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ የተከናወኑ አበይት ተግባራት እና የረቂቅ ስራቸው በመጠናቀቅ ላይ በሚገኙት የሽግግር ፍትሕ የሕግ ማዕቀፎች ላይ ገለጻዎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
የሁለቱም ተቋማት የስራ ኃላፊዎች በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ ባስተላለፉት መልዕክትም በቀጣይ በረቂቅ ሕጎች ላይ በሚካሄዱት የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረኮች ላይ በከፍተኛ ትኩረት ጥልቅ አስተያየቶችን በመስጠት ለህጎቹ ጥራት የበኩላቸውን ሚና መወጣት እንደሚኖርባቸው አጽዕኖት ሰጥተው ገልጸዋል፡፡
ፈጣን የመረጃ ልውውጥ እና ቋሚ የግንኙነት መስመር ለመዘርጋት እንዲቻልም የተቋማዊ ቅንጅታዊ አመራር መድረክ በመመስረት ወደ ስራ እንዲገባ እንደሚደረግም ተገልጿል፡፡