ከመንግሥት ተቋማት፣ ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፣ ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ ከሠራተኛ እና አሰሪዎች ኮንፌዴሬሽኖች፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰብዓዊ መብት ማዕከል የተወጣጡ 22 አባላትን ያቀፈው የባለሙያዎች ኮሚቴ ተዋቅሮ ወደ ስራ ገብቷል፡፡
ኮሚቴው የንግድ እና ሰብዓዊ መብት ድርጊት መርሃ ግብርን በማዘጋጀት እና ሲጸድቅም ተፈጻሚነቱን በመከታተል ሂደት ሙያዊ አስተዋጾ እንዲያበረክት ታስቦ የተዋቀረ ሲሆን በኮሚቴው ውስጥ የተካተቱት አባላት ከጉዳዩ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው መሆኑ ጥራቱን የጠበቀ ድርጊት መርሃ ግብር ለማዘጋጀት የበኩሉን ሚና ይጫወታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ኮሚቴውን በሰብሳቢነት የሚመራው የፍትሕ ሚኒስቴር ከዳኒሽ የሰብዓዊ መብት ተቋም ጋር በመሆን ሀምሌ 24 ቀን 2016 ዓ.ም ባዘጋጀው የውይይት መድረክ መሠረት ኮሚቴው የመጀመሪያውን ውይይት አካሂዷል፡፡
በውይይቱ የተባበሩት መንግስታት የንግድ እና ሰብዓዊ መብት ድርጊት መርሃ ግብር የመርሆዎች መመሪያ፣ የንግድ እና ሰብዓዊ መብት በኢትዮጵያ፣ የሰብዓዊ መብት ድርጊት መርሀ ግብር አስፈላጊነት እና የባለሙያዎች ኮሚቴው ዓላማ እና ተልዕኮ ምንነትን የሚመለከቱ ገለጻዎች የቀረቡ ሲሆን በቀጣይ በንግድ እና ሰብዓዊ መብት ዙሪያ ለሚካሄደው ዳሰሳ ጥናት የተዘጋጀው መነሻ ሪፖርትም ለአባላቱ ቀርቧል፡፡
በቀረቡት ገለጻዎች ላይ የተለያዩ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች በአባላቱ ተነስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
ግንቦት 8 ቀን 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሂልተን ሆቴል መንግስታዊ እና መንግሰታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት በተካሄደ የማስጀመሪያ መድረክ የንግድ እና ሰብዓዊ መብቶች ድርጊት መርሃ ግብሩ ዝግጅት በይፋ መጀመሩ የሚታወስ ነው፡፡