በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የፍትሕ ሚኒስቴር፣ የንቃተ ሕግ፣ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት በኮንስትራክሽን የሕግ ማዕቀፎች፣ በውል አስተዳደርና ከኮንስትራክሽ ጋር በተያያዙ የሙስና ወንጀሎች ዙሪያ በዘርፉ ለሚሰሩ ዐቃብያነ ሕግ ሥልጠና እየሰጠ ነው::
ሥልጠናውን የሚሰጡት የሕግ አማካሪና ጠበቃ እንዲሁም በአዲስ አበባ ዩኒቭርስቲ በሕግ ትምህትር ቤት የኮንስትራክሽ ሎው መምህር የሆኑት አቶ ፋሲል ታደሰ እንደተናገሩት የሥልጠና ዓላማ የተቋሙ ዐቃብያነ ሕግ ከኮንስትራክሽን ጋር የተያያዙ የሕግ ማዕቀፎች፣የውል አስተዳደር እና በኮንስትራክሽን ዙሪያ ያሉ የሙስና ወንጀሎችን፣ የማስረጃ አሰባሰብ፣ትንተና እና ክስ አቀራረብ ላይ ያላቸውን ክህሎትና እውቀት ለማዳበር ነው ብለዋል፡፡ አክለውም የሥልጠናውን ዓላማ ለማሳካት አንድ የግንባታ ፕሮጄክት ከታሰበበት አንስቶ ተጠናቆ ለታቀደለት ዓላማ እስከሚውልበት ድረስ ባለው ሂደት የሚከናወኑትን ተግባራቶች፣በተለያዩ መንገድ እና ግንኙነት በሂደቱ የሚሣተፉትን ወገኖች እና እነዚህኑ ተግባራቶችን እና ተሣታፊ ወገኖችን የሚገዙትን የሕግ ማዕቀፎችን መገንዘብ ያስፈልጋል ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ሥልጠናው ከኮንስትራክሽን ጋር የተያያዙ የሕግ ማዕቀፎች፣ የኮንስትራክሽን ውል አስተዳደር ምንነት እና ይዘት፣ በኮንስትራክሽን ዘርፍ ያሉ የሙስና ወንጀሎች እና የማስረጃ አሰባሰብ፣ ትንተና እና ክስ አቀራረብ ሂደቶች ላይ ትኩረቱን አድርጎ እየተሰጠ ይገኛል፡፡ በዘርፉ የሚሰሩ ዐቃብያነ ህጎች ሥልጠናውን እየተከታተሉ ሲሆን ሥልጠናው ዛሬን ጨምሮ ለ3 ተከታታይ ቀናት የሚቀጥል ይሆናል፡፡