የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የመንግሥት ሕግ እና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ በላይሁን ይርጋ በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ከሆኑትን ሚስተር ሺባታ ሂሮኖሪ ጋር በሽግግር ፍትሕ ትግበራ ምዕራፍ ሂደት የጃፓን እና የኢትዮጵያ መንግሥት በጋራ ስለሚሰሩበት ሁኔታ ውይይት አድርገዋል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ በላይሁን ይርጋ እኤ.አ ከ1930ዎቹ ጀምሮ በኢትዮጵያ እና በጃፓን መካከል ተገንብቶ የቆየው የዲፕሎማሲ ግንኙነት ሀገራቱ በግብርና፣ በጤና፣ በትምህርት፣ ማኑፋክቸሪንግ እና መሰል ዘርፎች ዙሪያ በጋራ ለመሥራት እንዳስቻላቸው አስታውሰው የጃፓን መንግሥት ለኢትዮጵያ ላበረከተው አስተዋጽኦ ምስጋናቸውን አቅርበው ግንኙነቱ በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታው አክለውም ኢትዮጵያ ባለፉት ጊዜያት የተፈጸሙትን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ለመጨረሻ ጊዜ እልባት ሰጥቶ በቀጣይ ዘላቂ ሰላም፣ ዴምክራሲ እና የሕግ የበላይነትን ለማስፈን የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ጸድቆ ወደ ትግበራ በመግባቱን አስታውሰው የፖሊሲ ዝግጅቱ ሂደት አሳታፊ እና ግልጽ እንደነበረ አክለው ለአምባሳደሩ ገልጸዋል፡፡
የፖሊሲውን መጽደቅ ተከትሎም የፖሊሲ ትግበራ ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ ወደ ትግበራ እንደገባ ገልጸው በአሁኑ ጊዜም የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ላይ የተመላከቱትን ማስተግበሪያ ስልቶቹን የሚተገብሩትን ተቋማት ለማቋቋም የሚያስችሉ የሕግ ማዕቀፎች በመዘጋጀት ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ አያይዘውም በሕግ ረቂቆቹ ላይ የሚደረጉትን የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረኮችን ጨምሮ በፖሊሲ ትግበራ ፍኖተ ካርታው ላይ የተመላከቱትን ተግባራት በመተግበር ሂደት የጃፓን መንግሥት ከኢትዮጵያ በጋራ እንዲሰራ ተስፋ አድርጋለውም ብለዋል፡፡
የጃፓን አምባሳደር ሚስተር ሺባታ ሂሮኖሪ በበኩላቸው ሀገራቸው ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ያላት የረጅም ጊዜ የዲፕሎማሲ ግንኙነት በሀገራቱ መካከል ጠንካራ ወንድማማችነት መፍጠሩን አውስተው የአንድ ሀገር እድገት እና ልማት የሚረጋገጠው ዘላቂ ሰላም ሲኖር በመሆኑ ይህንኑ ለማረጋገጥ ሀገሪቱ የምትተገብራቸው ፕሮግራሞች ውጤታማነትን ለማረጋገጥ በሚደረግ ጥረት ውስጥ የጃፓን መንግሥት ተገቢውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡ አምባሳደሩ አክለውም የሽግግር ፍትሕም ሰላምን ለማረጋገጥ እና ዴሞክራሲን ለማስፈን ከሚረዱ ዘዴዎች መካከል አንዱ እና ዋነኛው በመሆኑ ሀገራቸው ሂደቱን እንደምትደግፍ አረጋግጠዋል፡፡
በመጨረሻም በቀጣይ የትብብር ስራው የሚመራበትን ሰነድ ለማዘጋጀት እና ለትግበራ ሂደቱ ተገቢውን ድጋፍ እና ክትትል ለማድረግ ስምምነት ላይ ተደርሶ ውይይቱ ተጠናቋል፡፡
በውይይቱ የሽግግር ፍትሕ የተቋማት ቅንጅታዊ አመራር ሴክሬታሪያት ኃላፊ እና የባለሙያዎች ቡድን አባላት ተገኝተዋል፡፡