የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እ.ኤ.አ መጋቢት ፳፩ ቀን ፪ሺ፲፰ ዓ.ም በሩዋንዳ ኪጋሊ በተደረገው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ የተፈረመውን የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ማቋቋሚያ ስምምነትን በአዋጅ ቁጥር ፩ሺ፩፻፳፬/፪ሺ፲፩ ያጸደቀው በመሆኑ፤
የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በ፲፫ኛ ልዩ ስብሰባው አባል ሀገራት በጸደቀው የታሪፍ ድርድር ዘዴ በተመለከተው የጊዜ ሰሌዳ ውስጥ ስምምነት በሚደረስባቸው የታሪፍ መስመሮች ላይ የሚጣለው ቀረጥ ነጻ እንዲሆን በሚያስችል አኳኋን በየዓመቱ ሊደረግ የሚገባውን የታሪፍ ቅነሳ የሚያሳይ የታሪፍ ቅነሳ ሰንጠረዥ እንዲያወጡ የወሰነ በመሆኑ፣ እና አባል ሀገራት በታሪፍ ቅነሳ ሂደት አንዱ ከሌላው ጋር የሚያደርጉት የንግድ ልውውጥ በዕቃ አይነት ሽፋን እና በታሪፍ ቅነሳ ረገድ ስምምነት ከተደረሰበት ዘዴ ጋር የተጣጣመ እና የሰጥቶ መቀበል መርህን መሰረት ያደረገ ሊሆን እንደሚገባ የወሰነ በመሆኑ፤
ኢትዮጵያ ከአባል ሀገራት ጋር በሚኖራት የዕቃ ንግድ ላይ ተፈጻሚ የሚሆነውን የታሪፍ መጣኔ ለሌሎች አባል ሀገራት ቀርቦ እ.ኤ.አ የካቲት ፲፯- ፳፩ ቀን ፪ሺ፳፬ ዓ.ም በተደረገው የመሪዎች ጉባኤ የጸደቀ ሲሆን የቀጠናው አባል ሀገራት ከሌሎች አባል ሀገራት ለሚመጡ ዕቃዎች የሚያደርጉት የታሪፍ ቅነሳን የዕቃዎች የቀረጥ ቅነሳ ሰንጠረዥ በማዘጋጀት ተቀባይነት ባለው የሀገር ውስጥ የነጋሪት ጋዜጣ አሳትመው እንዲያሳውቁ እና ይህም የዕቃዎች ንግድ ፕሮቶኮል አባሪ መሆኑ በአህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ማቋቋሚያ ስምምነቱ የተደነገገ በመሆኑ፤
የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነትን ለማጽደቅ በወጣው አዋጅ ቁጥር ፩ሺ፩፻፳፬/፪ሺ፲፩ እና በተዋሃደ የሸቀጦች አሰያየምና አመዳደብ ስርዓት ኮንቬንሽን ማጽደቂያ አዋጅ ቁጥር ፷፯/፩ሺ፱፻፹፭ (እንደተሻሻለ) አንቀጽ ፬ መሰረት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ይህን ደንብ አውጥቷል።
•
•