ባንኮች ገንዘብ በማሰባሰብ እና ወደ ተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች በማሰራጨት ለኢኮኖሚ ልማት ወሳኝ ሚና የሚጫወቱ በመሆናቸው እና በሀገሪቱ ኢኮኖሚ የክፍያና የሒሳብ ማወራረድ ሥርዓት ውስጥ ቁልፍ ቦታ የሚይዙ በመሆኑ በጥንቃቄ በተዘጋጀ የሕግ እና የቁጥጥር ማዕቀፍ መሠረት የባንክ ዘርፍን ለውጭ ኢንቨስትመንት ክፍት ማድረግ የዘርፉን ተወዳዳሪነትና ውጤታማነት በማሻሻል ለዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ የሚታመን በመሆኑ፤
አዋጭነቱ ያበቃ እና መልሶ አዋጭ የመሆን ተስፋ ተደርጎ ለሚቆጠር ማንኛውም ባንክ ከፍተኛ የሥርዓት መናጋትን እና ኪሳራን በማያስከትል መልኩ እልባት ለመስጠት አስፈላጊ የሆኑ በርካታ የተለያዩ ሥልጣኖችን እና አማራጮችን ለእልባት ሰጪ ባለሥልጣን አካሉ ማለትም ለብሔራዊ ባንክ የሚሰጥ ውጤታማ የእልባት ሥርዓት መኖር አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤
የባንክ ሥራ በአግባቡ ካልተመራ በፋይናንስ ሥርዓቱና በማክሮ ኢኮኖሚው ላይ ያለመረጋጋትን ሊያስከትል የሚችል በመሆኑ፤
የፋይናንስ ሥርዓትና የማክሮ ኢኮኖሚ ያለመረጋጋት ሕዝብ እና መንግሥትን ከፍተኛ ዋጋ የሚያስከፍል በመሆኑ፣
የባንክ ዘርፍ ፈቃድ አሰጣጥንና ቁጥጥርን በሚመለከት አሁን ካለው እና ወደፊት ከሚኖረው የዘርፉ ለውጥ ጋር የሚጣጣም የተሟላ የሕግ ማዕቀፍ በመዘርጋት የባንክ ሥራን ደህንነት፣ ጤናማነትና መረጋጋት ቀጣይነት ባለው መልኩ ማረጋገጥ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤
በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 6 51 (1) መሠረት የሚከተለው ታውጇል፡፡
•
•