በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነ የንግድና ሰብዓዊ መብት ብሄራዊ የድርጊት መርሀ ግብር ዝግጅት ላይ ትኩረት ያደረገ ወርክሾፕ ተካሄደ

Workshop Held Focusing on the Preparation of Ethiopia's First National Action Plan on Business and Human Rights

በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ብሔራዊ የሰብዓዊ መብት መከታተያ ዳሬክቶሬት፣ ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እና The Danish Institute For Human Right ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነ የንግድና ሰብዓዊ መብት ብሔራዊ የድርጊት መርሀ ግብር ዝግጅቶች ላይ ያተኮረ ወርክሾፕ ተካሂዷል፡፡

ከተለያዩ የአለም ሀገራት የመጡ ባለድርሻ አካላት በተሳተፉበት መድረክ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የሲቪል፣ ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማኅበራዊ መብቶች ኮሚሽነር ክቡር ዶ/ር አብዲ ጅብሪል ተቋማቸው የሰብዓዊ መብት ጉዳዮችን የመከታተልና ግብረ መልስ የመስጠት የገለልተኝነት ሚና ያለው መሆኑን አስታውሰው፤ የተለያዩ ዓለም ዓቀፍ ተቋማትና የውጪ ሀገራት ማኅበረሰብ ኢትዮጵያ ብሔራዊ የንግድና ሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሀ ግብር እንዲኖራት በተደጋጋሚ እየጠየቁ በመሆኑ እንዲሁም ለጉዳዩ ትኩረት መስጠትና ለማህበረሰቡ ግንዛቤን የመፍጠር ስራን ማከናወን አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ኮሚሽኑ ከፍትሕ ሚኒስቴርና ከሚመለታቸው አካላት ጋር በመተባበር የሚጠቅበትን አስተዋጽኦ ለማበርከት ዝግጁ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በኢ.ፌ.ዲሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የመንግሥት ሕግና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ በላይሁን ይርጋ በመድረክ መክፈቻ ንግግራቻው ወቅት እንደገለፁት፤ ብሔራዊ የድርጊት መርሀ ግብር ዝግጅቱ ዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት መስፈርቶችን ከንግድ ጋር ማስተሳሰር የተቻለበት ወሳኝ ደረጃ ላይ መደረሱን አመልካች መሆኑን ገልፀው፤ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ላይ በሚገኝ እንደ ኢትዮጵያ ባለ ሀገር ንግድና ሰብዓዊ መብትን አስተሳስሮ መጓዝ እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ፤ በሰብዓዊ ክብር፣ በሠራተኛ መብት፣ በአካባቢ ጥበቃና፣ ከንግድ ጋር ተያይዞ ለተጎዱ መፍትሄ በመስጠት ረገድ ብሔራዊ የድርጊት መርሀ ግብሩ ከኢኮኖሚ እድገቱ ጋር ተደጋግፎ እንደሚሄድ ማረጋገጥ የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል፡፡

አክለውም ብሔራዊ የንግድና ሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሀ ግብር ኃላፊነትና ተጠያቂነት ያለበት የአሠራር ስርዓትን የሚከተል የንግድ እንቅስቃሴን በመፍጠር የመብት ጥሰቶችን የመከላከል ዓላማ ያለው መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህ ታሪካዊ የዝግጅት ተግባር ላይ ከጅምሩ አንስቶ በመሳተፍ የቴክኒክ እንዲሁም የፋይናንስ ድጋፍ ያደረጉ ባለድርሻ አካላትን አመስግነው፤ መንግሥት ብሔራዊ የንግድና ሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሀ ግብር እንዲዘጋጅ ብቻ ሳይሆን ተግባራዊ ተደርጎ ውጤት እንዲያመጣ ለማድረግ ጠንካራ እምነት ያለው መሆኑን አመላክተዋል፡፡

የThe Danish Institute For Human Right ተወካይ አሊስ ሙንሌይ በበኩላቸው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባስቀመጣቸው መስፈርቶች መሠረት በአለም ላይ 36 ሀገራት የንግድና ሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሀ ግብር አዘጋጅተው ተግባራዊ እያደረጉ መሆኑንና ከዚህም ውስጥ ከአፍሪካ ኬንያ፣ ዑጋንዳ፣ ናይጄሪያ እና ጋና እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት 5 የአፍሪካ ሀገራት ብሔራዊ የድርጊት መርሀ ግብራቸውን በማዘጋጀት ላይ መሆናቸውን ጠቅሰው ኢትዮጵያም የድርጊት መርሀ ግብሩን ለማዘጋጀት መነሻ የሆነውን Baseline /Assessment Plan/ መነሻ ግምገማ ረቂቅ በማዘጋጀት ከዓለም ዓቀፍ የተለያዩ ተቋማት ተወካዮችና ከንግድና ሰብዓዊ መብት የቴክኒክ ኮሚቴ አባላት ጋር ውይይቶችን እያደረጉ መሆናቸውን ገልፀው፣ የንግድና ሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሀ ግብር በትክክል ተግባራዊ እንዲሆን ካስፈለገ የመንግሥትን የመሪነት ሚና፣ ግልጽነትን፣ እንዲሁም የባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ አመልክተው በዚህ ረገድ ተቋማቸው አስፈላጊ የሆነ ድጋፍ ማድረጉን እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

በመድረኩም በፍትሕ ሚኒስቴር የብሔራዊ የሰብዓዊ መብት መከታተያ ዳሬክቶሬት አስተባባሪነት በመከናወን ላይ የሚገኙ የንግድና ሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሀ ግብርን ለማዘጋጀት በተከናወኑ የቅድመ ምልከታ የዳሰሳ ጥናቶች መሠረት የተገኙ ውጤቶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

በተጨማሪም በመድረኩ ላይ የድርጊት መርሀ ግብር አዘጋጅተው ተግባራዊ ማድረግ የጀመሩት ኬንያ እና ዑጋንዳ በበይነ መረብ እንዲሁም ረቂቁን በማፀደቅ ሂደት ላይ የሚገኙት የጋና ተወካይ ያላቸውን ልምድ እንዲያካፍሉ ተደርጓል፡፡ በአጠቃላይ ዓለም ዓቀፍ መስፈርቶችን ያሟላ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የንግድና ሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሀ ግብር እንዲዘጋጅ ለማድረግ የሚያስችሉ ቀዳሚ የሆኑ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑ ለሁለት ቀናት በቆየው ወርክሾፕ ላይ ተመላክቷል፡፡

Tagged Under: Accountability action business Business and Human Rights civil and political rights corporate social responsibility diligence due engagement Ethiopian Human Rights Commission federal democratic republic of ethiopia (fdre) ghana human human rights due diligence International Standards kenya ministry of justice (ethiopia) National national action plan nigeria plan Rights stakeholder Stakeholder Engagement Transparency uganda workshop
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች

ተመሳሳይ ዜናዎች