የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ከሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አጋር ከሆኑ ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የተዘጋጀና ትኩረቱን መደበኛ ባልሆነ መንገድ ከአገር ለመውጣት ሲሞክሩ የሚያዙ ዜጎችን ወደ አካባቢያቸው ለመመለስ የተፈጸመ የቅብብሎሽ መግባቢያ ሰነድ የትግበራ ማስጀመሪያ የውይይት መድረክ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
ከሚያዝያ 08-10 2018ዓ.ም የሚካሄደው ይህ መድረክ መደበኛ ባልሆነ መንገድ ከአገር የሚወጡና ለተለያዩ ችግሮች ተጋላጭ የሚሆኑ ዜጎችን ተቀብሎ ወደ አካባቢያቸው እንዲመለሱ ለማድረግ በተቋማዊ ወይም በአካባቢያዊ ገደቦች ምክንያት የከፋ የሰብዓዊ መብት ጥቃትና ጉዳት እንዳያጋጥማቸው ለማስቻል በፌዴራል ተቋማትና በክልሎች መካከል የተፈረመው ብሔራዊ የትብብር ጥምረት የመግባቢያ ሰነድ ትግበራን በሚመለከት እስካሁን ያለበትን ደረጃ ገምግሞ የመግባቢያ ስምምነቱን በተጠናከ መንገድ ወደ ተግባር ለመለወጥ፣ ለትግበራው ኃላፊነት ያለባቸውን ባለሙያዎችና አመራሮችን አቅም የማጠናከር፣ እንዲሁም የቅብብሎሽ ሂደቶች ቀልጣፋ፣ ወቅታዊና ለፍልሰተኞች ፍላጎት ምላሽ የሚሰጡ መሆናቸውን የማረጋገጥ አላማ እንዳለው ተመላክቷል፡፡
መደበኛ ባልሆነ መንገድ ፍልሰት በሚካሄድባቸው በጅቡቲ ሶማልያ ወደ አረብ አገራት፣ ከደቡብ ኢትዮጵያ ተነስቶ ወደ ደቡብ አፍሪካ፣ በቶጎ ውጫሌ እንዲሁም በሰሜን መተማ በኩል ወደ አውሮፓ ለመድረስ በሚደረጉ ፍልሰት መስመሮች ላይ የሚያዙ ዜጎችን ተቀብሎ በብሔራዊ የትብብር ጥምረት ስምምነቱ መሰረት ወደ አካባቢያቸው እንዲመለሱ ማድረግ በተለይም በአሁኑ ወቅት በመካከለኛው ምስራቅ አካባቢ እየተካሄደ ካለው ወቅታዊ የሰላምና ጸጥታ ስጋት ዜጎችን መጠበቅ እንደሚገባ ተገልጻል፡፡
ኢትዮጵያ የፍልሰት መነሻ፣ መተላለፊያ እና መዳረሻ አገር በመሆኗ በተለይ የተመላሾች ቁጥር እየጨመረ የመጣ በመሆኑ የተቀናጀ የምላሽ አሰጣጥ የቅብብሎሽ ሥርዓትን ማበጀት ይገባል፡፡ በሌላ በኩል የትብብር ጥምረቱን ክፍተቶች በጥናት እየለዩ መፍትሔ መስጠት የሚያስፈልግ መሆኑ የተመለከተ ሲሆን ይህ የትብብር ጥምረት አገራዊ ስምምነት ሆኖ በከፍተኛ የፌዴራል እና የክልል ኃላፊዎች መካከል የተፈረመ በመሆኑ የቅንጅቱን ተግባራዊነት አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡
በቀጣይነት በስምምነቱ ትግበራ መሠረት በቂ የሆነ ቅድመ ዝግጅት አድርጎ ሥራዎችን ማከናወን በተለይ ተጋላጭ የሆኑ ሴቶችና ህጻናት አያያዝ ሁኔታን በተመለከተ ትኩረት መስጠትና እየተወያዩ ችግሮችን በጋራ መፍታት የሚያስፈልግ መሆኑ የተወሳ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ይህ አገራዊ ተግባር በመንግስት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራበት ያለ በመሆኑ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በዚያው ልክ ለሥራው ተገቢውን ትኩረት ሰጥተው ኃላፊነትን መወጣት እንዲሁም በፋይናንስና ሌሎች መስኮች ላይ ድጋፍ ለማድረግ መስራት እንደሚገባ ተመላክቷል፡፡
በመድረኩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ከአዲስ አበባ፣ አፋር፣ አማራ፣ድሬደዋ፣ ኦሮምያ፣ሶማሌ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክሎሎች የተወከሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ ፖሊስ ኮሚሽነሮች፣ የሕግ ባለሙያዎች፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተሳታፊ ሲሆኑ፤ በቀጣይ ቀናት ለትብብርና ጥምረት የቴክኒክ ባለሙያዎች ተያያዥነት ያለው አጋዥ የክሕሎት ማዳበሪያ ሥልጠና የሚሰጥ ይሆናል፡፡