በኢ.ፌ.ዴ.ሪ የመከላከያ፣ የፍትሕ እና የሰላም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች የክረምት በጎፍቃድ አረንጓዴ አሻራን የማኖር ችግኝ ተከላ መርሀ-ግብር ተካሄደ

Winter Green Seedling Preservation Campaign Launched by the FDRE Ministries of Defense, Justice, and Peace

የመከላከያ፣ የሰላም እና የፍትሕ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች እና ተጠሪ ተቋሞቻቸው የክረምት በጎ ፍቃድ ተግባራት አንዱ ክፍል የሆነው የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሀ-ግብር በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ሉሜ ወረዳ ላይ ተከናውኗል፡፡

“በመትከል ማንሰራራት” በሚል መሪ ቃለ የ2017 ዓ.ም የክረምት በጎ ፍቃድ አረንጓዴ አሻራን ማኖር በሚለው መርሀ-ግብር መሠረት ሶስቱ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች እና ተጠሪ ተቋሞቻቸው የችግኝ ተከላ ስነስርዓት፣ ለተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁሶችን የመለገስ እንዲሁም አቅም ለሌላቸው ወገኖች ቤት መገንቢያ ቦታን በመረከብ የመሠረት ድንጋይ የማስቀመጥ ሥነሥርዓት ተከናውናል፡፡

የዕለቱን መርሀ-ግብር የመከላከያ፣ የሰላም እና የፍትሕ ሚኒስትሮች፣ ሚኒስትር ዴኤታዎች እና የተጠሪ ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም ሰራተኞች በተገኙበት በተካሄደው በዚህ አረንጓዴ አሻራን የማኖር ዝግጅት ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኤፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ኢንጂነር አይሻ መሐመድ ዛሬ የሚተከለው ችግኝ ብቻ ሳይሆን የሀገር ተስፋ፣ የሀገር ግንባታ፣ የቃልኪዳን ዘር ይሆናል ያሉ ሲሆን “በመትከል ማንሰራራት” የሚለው መርህ የመንግሥት የድርጊት ጥሪን የሚያመለክት፡ ማንሰራራት በስራ፣ በእልህ፣ በትጋት የሚመጣ ውጤት መሆኑን የሚያሳይ እንደሆነ ገልዋል፡፡

ክብርት ሚንስትሯ አያይዘውም በዚህ የክረምት መርሀ-ግብር በአጠቃላይ ሶስቱ ሚንስቴር መስሪያ ቤቶች 18 ሚሊዮን ችግኞችን በተለያዩ መርሀ ግብሮች ለመትከል መዘጋጀታቸውን አስታውሰው÷ የመከላከያ ሰራዊቱ የሀገርን ድንበር ከማስከበር በላይ በያለበት አካባቢ ችግኞችንም በመትከል የልማት አሻራውን እንደሚያኖር ገልፀው በአጠቃላይ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ለሌሎች የሚተርፍ፣ የሚያድግና የሚያብብ በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ልብ ውስጥ መልካም ነገሮችን የሚያፀድቅ የአንድነት እና የሰላም አሻራ የሚቀመጥበት ነው ብለዋል፡፡

በሶስቱም ሚንስቴር መስሪያ ቤቶች አማካይነት በመከናን ላይ የሚገኘው የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ሉሜ ወረዳ ለሚገኙ 1500 ሕፃናት ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁሶች ድጋፍ የተደረገ ሲሆን በዚህ መርሀ-ግብር ላይ በመገኘት መልዕክት ያስተላለፉት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሐና አርዓያስላሴ አረንጓዴ አሻራ እንደ መንግሥት በተግባር ሀገርን እናሻግራለን የሚል መልዕክትን የያዘ እና ይህም በተጨባጭ የተገለፀበት መሆኑን አውስተው የወደፊት የሀገር ተስፋ ለሆኑ ልጆች የደብተር ድጋፍ መደረጉም ይህን መሰል የበጎ ፍቃደኝነት ስራን በቀጣይነት አጠናክረን እንድንቀጥል የሚያደርግ በመሆኑ በጎነትን ማስቀጠል እንዲሁም ክረምቱን በሙሉ በተለያዩ መርሀ ግብሮች ላይ በመሳተፍ የታሰበውን ግብ ለማሳካት መሥራት እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡

ለዕለቱ በተያዘው መርሀ ግብር መሠረት በሉሜ ወረዳ ለሚገኙ አቅም ለሌላቸው ወገኖች መኖሪያ ቤት መገንቢያ የሚሆን ቦታ ከወረዳ አስተዳደሩ በመረከብ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶቹ አመራሮች እና የተጠሪ ተቋሞቻቸው ከፍተኛ ኃላፊዎች በተገኙበት የመሠረት ድንጋይ የማኖር ስነስርዓት ተከናውኗል፡፡ ቀጥሎም አረንጓዴ አሻራን በማኖር ፕሮግራም ላይ የተሳተፉ ከፍተኛ አመራሮች አቮካዶን ኤክስፖርት በማድረግ በምትታወቀው በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ሉሜ ወረዳ ቆቃ ቀበሌ በመገኘት በመንግሥት ድጋፍ ተሰርተው ወደ ተግባር ከገቡት የማኅበረሰብ አቀፍ የፍትሕ ማዕከላት አንዱ የሆነውን የጎበኙ ሲሆን፤ ይህም ፍትሕ ወደ ህዝቡ የበለጠ እንዲቀርብ በማድረግ መደበኛ ባልሆነ መንገድ በባህላዊ ስርዓት የእርቅና የፍትሕ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኘው ማዕከል በ2017 ዓ.ም ብቻ ከ222 በላይ ጉዳዮችን ተመልክቶ የማስታረቅና የማስማማት ስራዎችን በማከናወን 1.2 ሚሊዮን ብር እንዲሁም የተለያዩ የቀንድና የጋማ እንሰሳትን ለባለቤቶቻቸው ከማስመለስ በተጨማሪም የቤተሰብ ጉዳዮችን ተመልክቶ እንዲፈቱ የማድረግ ስራ ማከናወኑን ለመረዳት ተችሏል፡፡.

የቅርብ ጊዜ ዜናዎች

ተመሳሳይ ዜናዎች