በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የንቃተ ሕግ፣ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት ከጀስቲስ ፎር ኦላ ፕሪዝን ፌሎሺፕ ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር በታክስና ጉምሩክ ወንጀሎች ዙሪያ ከሁሉም ክልሎች ለተወጣጡ ዐቃቤያነ ሕግ ያዘጋጀው ሥልጠና ከህዳር 27 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በአዳማ ከተማ እየተሰጠ ይገኛል።
በሥልጠናው መክፈቻ ላይ ተግኝተው ንግግር ያደረጉት በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የተቋም ግንባታ እና ሪፎርም ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ኤርሚያስ የማነብርሃን እደገለፁት ሥልጠናው የክልል ፍትሕ አካላትን አቅም ለማሳደግ እንዲሁም ፍትሕ ሚኒስቴር ከክልሎች ጋር ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ያሰበ ነው። አክለውም የኢኮኖሚ ወንጀሎች በተለይም የታክስና ጉምሩክ ወንጀል በሀገር እና ሕዝብ ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ ዐቃቤያነ ሕግ የነዚህን ወንጀሎች ምንነት፣ ባህሪ እና የአፈፃፀም ሁኔታ፣ ሕግጋቱን እና አተገባበራቸውን በተገቢው ተገንዝበው ወንጀሎቹን በመመርመር እና ክስ መስርተው ጥፋተኞችን ለማስቀጣት እንዲችሉ የሚረዳ መሆኑን ገልፀዋል። በተጨማሪም የፍትሕ ተቋማትን እና ባለሞያዎች አቅም ማጎልበት በፍትሕ ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን እቅዱ ትኩረት እንደተሰጠው እና ይህም ሥልጠና የዛው አካል እንደሆነ ገልፀዋል። በመጨረሻም ሥልጠናውን ለመስጠት እንዲቻል ድጋፍ ላደረገው ጀስቲስ ፎር ኦል ኢትዬጵያ ምስጋና አቅርበዋል።
በሌላ በኩል በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የንቃተ ሕግ፣ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ እንዳልካቸው ወርቁ ባለፉት አመታት በተለያዩ የሕግ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ለክልል ዐቃቤያነ ሕግ ሥልጠናዎች መሰጠታቸውን አስታውሰው የአሁኑ ሥልጠናም የተዘጋጀው ከሥልጠና ፍላጎት ዳሰሳ ጥናት በመነሳት መሆኑን ገልፀዋል።
በሥልጠናው የገቢ ግብር፣ የተጨማሪ እሴት ታክስ፣ እክሳይዝ ታክስ እና ጉምሩክ ሕግጋት እንዲሁም ሕግጋቱን በመተላለፍ የሚፈፀሙ ወንጀሎች በሰፊው የሚዳሰሱ ርዕሰ ጉዳዮች መሆናቸው ተጠቁሟል።