የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በጋራ በሚሰሩባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ተወያየ

Ministry of Justice and Addis Ababa Police Commission Discuss Collaborative Efforts on Key Issues

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የፍትሕ ሚኒስቴር ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በጋራ በሚሰሩባቸው ጉዳዮች ዙሪያ በዛሬው ዕለት ውይይት አድርጓል፡፡

በፍትሕ ሚኒስቴር የተቋም ግንባታና ሪፎርም ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ክቡር ኤርሚያስ የማነብርሀን (ዶ/ር) በውይይት መድረኩ ተገኝተው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አመራሮችና ባለሙያዎች ላደረጉላቸው አቀባበል ምስጋናቸውን አቅርበው ፍትሕ ሚኒስቴር ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በፍትሕ ሚኒስቴር እየበለፀገ ያለውን የወንጀል አስተዳደር ስርዓት (CRIMS) እና በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን አስመልክቶ በቅንጅት መሥራት ለፍትሕ ዘርፉ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አንዳለው አውስተው፤ በተቋማቱ የሚበለፅጉ ሲስተሞችን ተጠቅሞ በፍትሕ ዘርፉ ተጨባጭ የሆነ ለውጥ ለማስመዝገብ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በፍትሕ ዘርፉ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራባቸው ከሚገኙ ተቋማት አንዱ የፖሊስ ተቋም መሆኑን ያወሱት ሚኒስቴር ዴኤታው ተቋሙ የወንጀል ተጠርጣሪዎችን ተከታትሎ ከመያዝ ጀምሮ እስከፍርድ ድረስ ያለውን ሂደት በቴክኖሎጂ በታገዘ መልኩ ማካሄዱ ለሌሎች ዓርአያነት ያለው ተግባር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ሚኒስቴር ዴኤታው አክለውም ፍትሕ ሚኒስቴር የሴቶችና ሕፃናትን አስመልክቶ በአገር አቀፍ ደረጃ መረጃ የሚያዝብት ፣የሚደራጅበት እና የሚጋራበት ዲጂታል ሲስተም እያለማ መሆኑን ጠቅሰው ከዚህም ጋር ተያይዞ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በቀጣይ በጋራ የሚሰሩ ስራዎች እንዳሉ አመላክተው ለኮሚሽኑ ከስራው ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ሥልጠናዎች እንደሚሠጥና ለወንጀል ምርመራ ስራ አስፈላጊ የሚሆኑ ቁሳቁሶችን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ምርመራ ክፍል ኃላፊ ክቡር ምክትል ኮሚሽነር ሀሰን ነጋሽ በበኩላቸው ፖሊስ መደራጀት ያለበትን ማስረጅ በአግባቡ ለማደራጀትና የፍትሕ ስርኣቱ የተሳለጠ እንዲሆን ለማስቻል እንዲሁም በሴቶችና ሕፃናትን ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ከመከላከል ጋር በተያያዘ ከፍትሕ ሚኒስቴር ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

በመጨረሻም ክቡር ኤርሚያስ የማነብርሀን (ዶ/ር) የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንን የስራ እንቅስቃሴ ተዘዋውረው የጎበኙ ሲሆን፣ የፍትሕ ሚኒስቴር ለኮሚሽኑ ለወንጀል መከላከል ስራ አጋዥ የሚሆኑ የኮሚፒዩተር ድጋፍ ርክክብ በማድረግ መድረኩ ተጠናቋል፡፡

Tagged Under: Addis Ababa Police Crime Prevention
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች