ሥልጠናው የተሰጠው ከአዲስ አበባ አስራ አንዱም ክፍለ ከተሞች ለተውጣጡ የሕብረተሰብ ተወካዮች ነው፡፡ ሥልጠናው በአስራ አንዱም ክፍለ ከተሞች ላይ ከክፍለ ከተማ ነዋሪዎች ፎረም፣ ከሴቶች ማህበር፣ ከእድሮች ህብረት፣ ከወጣቶች ማህበር፣ ከአካል ጉዳተኞች ማህበርና ከአረጋውያን ማህበር ለተውጣጡ 400 ለሚሆኑ የሲቪክ ማኅበረሰብ አደረጃጀት አባላት በሥልጠናው ላይ ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
የሥልጠናው ዋና ዓላማ የፍትሕ ተቋማት ያለ ህብረተሰቡ ዕገዛ፣ ተሳትፎ እና ድጋፍ ስራቸውን በአግባቡ ማከናወን እንደማይችሉ እና ማህበረሰቡ በየግዜው ከሚወጡ አዳዲስ የወንጀል መከላከል ህጎችና አሰራሮችን እንዲላመዱ ለማድረግ እና ውስብስብ የወንጀል ተግባሮች ስለሚፈጸሙበት መንገድ፣ ስለ ወንጀል መከላከል፣ ጥቆማ አሰጣጥና አቀራረብ እንዲሁም ከዚህ ጋር የተያያዙ የሕግ ድንጋጌዎች ይዘት ላይ ሰፊ ግንዛቤ ማስጨበጥ ነው፡፡
ሥልጠናው የተዘጋጀው በኢፌዲሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የንቃተ ሕግ፣ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት ከአስራ አንዱም ቅርንጫፍ ፅ/ቤቶች ጋር በመተባበር ሲሆን ሥልጠናውን የሰጡት በፍትሕ ሚኒስቴር የንቃተ ሕግ፣ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት ዐቃቢያነ ሕግ ናቸው፡፡ ሥልጠናው በይዘቱም በማህበረሰቡ ውስጥ ያሉ አደረጃጀቶች ወንጀልን ከመከላከል አኳያ ምን ምን ድርሻዎች እንዳላቸው፣ ህብረተሰቡ ከሕግ አንፃር ለፍትሕ እርዳታ ከመስጠት አንጻር ያለበትን ግዴታ፣ ወንጀልን የመጠቆምና ምስክር ሆኖ የመቅረብ ግዴታ እና የሕፃናት መብቶችን በሚመለከት ሰፋ ያለ ገለፃ ተደርጓል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ስለወንጀል ምንነት፣ የሀገሪቱ የወንጀል ሕግ ስላለው የመንግሥትንና ነዋሪዎችን ሰላምና ደኅንነት የማረጋገጥ ዓላማ እንዲሁም የማረምና የማስተማር ግቦች ተዳሰዋል፡፡
በሥልጠናው ለምስክሮችና ጠቋሚዎች ከለላ የሚሰጥበትን ህጋዊ ስርዓት እና ከባባድ በሆኑ እንደ የሙስና፣ በሀገር፣ በህገ መንግስቱና በመከላከያ ሰራዊቱ ላይ ጉዳት የሚያስከትሉ በሞት እና በፅኑ እስራት የሚያስቀጡ ወንጀሎችን ሲፈፀሙ፤ ሊፈፀሙ መሆናቸውንም መረጃ ያለው ማንኛውም ሰው የመጠቆም ግዴታ እንዳለበትና ይህንን ግዴታ አለመወጣት የሚያስከትለውን የሕግ ተጠያቂነትም የተዳሰሱ ርዕሰ ጉዳዮች ናቸው፡፡