የጸረ ሙስና ህጎች፣ የስራ አመራር እና የሽግግር ፍትሕ በሚሉ ፅንሰ ሀሳቦች ዙሪያ ከሁሉም ክልሎች ለተውጣጡ ዓቃቢያነ ሕግ የአስልጣኞች ሥልጠና በአዳማ ከተማ ዛሬ ጥቅምት ዐ1 ቀን 2ዐ16 ዓ.ም. መስጠት ተጀምሯል።
ሥልጠናው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር እና ጀስቲስ ፎር ኦል ፒ ኤፍ ኢትዮጵያ በጋራ በመተባበር የተዘጋጀ ነው፡፡
ፍትሕ ሚኒስቴር የሶስት ዓመት የፍትሕ ዘርፍ የትራንስፎርሜሽን እቅድ አዘጋጅቶና ከወራት በፊት ከክልሎች ጋር በመወያየት የራሳቸውን እቅድ አውጥተው ወደ ስራ መገባቱን በፍትሕ ሚኒስቴር የተቋም ግንባታና ሪፎርም ዘርፍ ሚኒስቴር ዲኤታ ዶክተር ኤርሚያስ የማነብርሃን በሥልጠናው መክፈቻ ባደረጉት ንግግር ገልፀዋል።
ሚኒስትር ዲኤታው አያይዘውም በእቅድ ከተያዙ ዋነኛ ግቦች መካከል ውጤታማ የሆነ የንቃተ ሕግ ሥልጠና አንዱ መሆኑን አስታውሰው ይህንኑ ግብ እውን ለማድረግ ሥልጠናው መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
በዚህም መሠረት በተመረጡ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የአቅም ግንባታ ለመስጠትም ክልሎች በመረጧቸው ርእሰ ጉዳዮች በመመስረት የጸረ ሙስናና የሽግግር ፍትሕ ላይ ሥልጠናው ተዘጋጅቷል ብለዋል።
በዚህ ሥልጠና እየተሳተፉ ያሉ ሰልጣኞች ሥልጠናው የአሰልጣኞች ሥልጠና መሆኑን ተረድተውና ወደ ክልላቸው ሲመለሱ ሌሎችን በማብቃት ረገድ ድርብርብ ኃላፊነት እንዳለባቸው አውቀው በከፍተኛ አትኩሮትና ተሳትፎ እንዲከታተሉ አሳስበዋል።
በመጨረሻም ሥልጠናው እንዲሳካ ድጋፍ ላደረገው ጀስቲስ ፎር ኦል ኢትዮጵያ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ሥልጠናው ከዛሬ ጀምሮ ለሚቀጥሉት ሶስት ቀናት የሚሰጥ ሲሆን በዛሬው ውሎውም የሙስና ምንነት፣የሕግ ማዕቀፎች፣የሙስና ወንጀል ፍሬ ነገሮች የሚሉና ተያያዥ ጉዳዮች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል።