የፌዴራል አስተዳደር ሥነ-ሥርዐት አዋጅን በተሻለ በመተግበር አስተዳደራዊ ፍትህን ለማስፈን የሚያስችል ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል

Training Being Provided to Better Implement the Federal Administrative Procedure Proclamation and Ensure Administrative Justice

የአስተዳደራዊ ፍትሕን ለማስፈን የተቀረፀው የፌዴራል አስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 1183/2012ን በተሻለ ለመፈጸም ይቻል ዘንድ የተጀመረው የግንዛቤ ማስጨበጫ ንቅናቄ ተጠናክሮ ቀጥሏል።

የአስፈጻሚ ተቋማት የፌዴራል አስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅን በተሻለ በመፈጸም የሕዝቡን አስተዳደራዊ ፍትሕ ጥያቄ በሚመልስ መልኩ መፈጸም እንዲችሉ በአዋጁ ዓላማ እና ይዘት ዙሪያ ለተለያዩ ተቋማት አመራሮች ሥልጠና በመሰጠት ላይ ይገኛል። በዚህም መሠረት ጥቅምት 15/ 2016 ዓ.ም ለጤና ሚኒስቴር እና ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተጠሪ ለሆኑ ተቋማት ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡

የሥልጠና መድረኩን በንግግር የከፈቱት የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ ስለአዋጁ ጠቀሜታ አብራርተው ሥልጠናው አዋጁን በደንብ ባለማወቅ የሚፈጠሩ ስህተቶችን በማረም በውሣኔ አሰጣጥና መመሪያ አወጣጥ ሂደት ለሕጉ በመገዛት የተሻለ ሥራ ለመሥራት ያግዛል ብለዋል፡፡

ሥልጠናውን የሰጡት በፍትሕ ሚኒስቴር የመንግሥት ሕግ እና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ ወ/ሮ ትብለጥ ቡሽራ በአዋጁ አተገባበር ላይ ለታዩ ክፍተቶች ዋና ምክንያት ሆኖ የተለየው የተቋማት የግንዛቤ ክፍተት መሆኑን ጠቁመው ሥልጠናው ይህንን ለመቅርፍ እንዲሁም ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሩን ለማብቃት የሚያግዝ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በአዋጁ በተዳሰሱ ጉዳዮች ስለ መመሪያ አወጣጥ ሂደት፣ ስለ አስተዳደራዊ ውሳኔ አሰጣጥ፣ በውሳኔ ላይ የሚቀርቡ አቤቱታዎች ስለሚስተናገዱበት አግባብ እንዲሁም በአዋጁ የተቀመጡትን ግዴታዎች አለማክበር የሚያሰከትለውን ውጤት እና በፍርድ ቤቶች ኃላፊነትና ሥልጣን ዙሪያ አማካሪዋ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ይህንን ተከትሎም በሥልጠናው ተሳታፈዎች በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተው በአዋጁ አጠቃላይ ዓላማ እና አተገባበር ላይ ከተስተዋሉ ክፍተቶች በመነሳት ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

የአስተዳደር ሥነ-ሥርአት አዋጁን በተሻለ ማስተግበር የሚያስችል ሥልጠና ለበርካታ የፌዴራል ተቋማት ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች እየተሰጠ ሲሆን ከዚህ ቀደም ለትምህርት ሚኒስቴርና ለሚኒስቴሩ ተጠሪ ለሆኑ ተቋማት እንዲሁም ለባህልና ስፖርት ሚኒስቴርና ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተጠሪ ለሆኑ ተቋማት አመራሮች ሥልጠና መሰጠቱ ይታወሳል፡፡

Tagged Under: 1183/2012 administrative administrative appeals administrative decision-making administrative justice Administrative Law Capacity Building compliance enforcement Education Ethiopian Government federal Federal Administrative Procedure Proclamation Government Officials judicial review Justice law Leadership Training learning Legal Training ministry of education ministry of health procedure proclamation proclamation no. 1183/2012 regulatory compliance Rule of Law skill development Training
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች