በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ብሔራዊ የስብዓዊ መብቶች መከታተያ ዳይሬክቶሬት የባለሙያዎች ቡድን የድሬዳዋ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያን ጨምሮ በስሩ ያሉትን የገንደ ቆሬ እና ጎሮ ፖሊስ ጣቢያዎችን ጎብኝቷል፡፡
ጉብኙቱ ዓላማ ያደረገው ከተጠርጣሪዎች ጋር ተያይዞ በመምሪያው እንዲሁም በፖሊስ ጣቢያዎቹ ከምርመራ ጀምሮ ያሉ የስብአዊ መብቶች ጥበቃና አያያዝ ምን እንደሚመስል ምልከታ ለማድረግ፤ የሚታዩ ችግሮች ካሉ ሊወሰድባቸው ስለሚገባቸው የዕርምት ዕርምጃዎች ላይ በጋራ ለመሥራት እና የታዩ መልካም ተሞክሮዎችን ቀምሮ ለሌሎች ለማጋራት እንደሆነ በፍትሕ ሚኒስቴር የብሔራዊ የስብዓዊ መብት ማስተባበሪያ ዳይሬክቶሬት ዳይክተር አቶ አወል ሱልጣን በጉብኝቱ ወቅት ተናግረዋል፡፡
ቡድኑ በመምሪያው እንዲሁም በሁለቱ የፖሊስ ጣቢያዎች ያሉ ተጠርጣሪዎችን የስብዓዊ መብቶቻቸውን ጥበቃና አያያዝን በተመለከተ ምን እንደሚመስል ያነጋገራቸው እንዲሁም ምልከታ ያደረገ ሲሆን፤ በመመሪያው እንዲሁም በጣቢያው የሚገኙ መርማሪ ፖሊሶችን የምርመራ ሂደታቸውንም መቃኘት ችሏል፡፡
ጉብኝቱን መሠረት በማድረግም ቡድኑ ከድሬዳዋ ከተማ አሰተዳደርር ፖሊስ መምሪያ የወንጀል ምርመራ ም/ጠቅላይ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ማኦ ተሸመ እና የፖሊስ ጣቢያዎቹ ሀላፊዎች ጋር ሰፋ ያለ ውይይት አድርጓል፡፡
በተያያዘ የቡድን አባላቱ በድሬዳዋ አሰተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን የለሙ የተለያዩ የቴክኖሎጂ ሲስተሞች አማካኝነት እየተስሩ ያሉ የወንጀል መከላከል ስራዎችን ፤ የፖሊስ የጥቆማ ማዕከል አገልግሎትን እንዲሁም ከ500 በላይ አባላት ያሉትና የወንጀል መከላከል ስራውን በማገዝ የሚሳተፉ ወጣቶችን እንቅስቃሴ ጎብኝቷል፡፡