በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የፍትሕ ሚኒስቴር እና በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቱር በመተባበር በአፍሪካ የሰዎች እና የሕዝቦች መብቶች ቻርተርን (ባንጁል ቻርተር) አስመልክቶ በተዘጋጀው ከ7ኛ – 10ኛ ያለው ወቅታዊ የአገራዊ የአፈፃጸም ረቂቅ ሪፖርት እና በአፍሪካ የሴቶች መብቶች ፕሮቶኮልን (ማፑቶ ፕሮቶኮል) አስመልክቶ በተዘጋጀው መነሻ አገራዊ የአፈጻፀም ረቂቅ ሪፖርት ላይ በተደረገው በዙሁ የግብዓት ማሰባሰቢያ የውይይት መድረክ ላይ የሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት እንዲሁም የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡
በውይይቱ ወቅት በረቂቅ ሪፖርቶቹ ዙሪያ በርካታ አስተያየቶችና ግብዓቶች የተሰጡ ሲሆን ምንም እንኳን ሪፖርቶቹ በሚሸፍኗቸው ጊዜያት ውስጥ በርካታ ተግባራት የተከናወኑ ቢሆንም መረጃዎች በበቂ ሁኔታ ተደራጅተው የሚያዙ ባለመሆናቸው እንዲሁም በመጠየቅ ላይ ያሉት መረጃዎች በወቅቱ በተሟላ ሁኔታ የማይላኩ በመሆናቸው ሪፖርቶቹ በብዙ ዘርፎች ላይ ክፍተት እንደሚታይባቸው ተነስቷል፡፡
በዚህም መሠረት በቀጣይ የሚመለከታቸው ሁሉ መረጃዎችን በአጭር ጊዜ እንዲልኩና ሪፖርቶቹ በተሻለ ደረጃ ተጠናቅረው እንዲላኩ ሁሉም ኃላፊነቱን እንዲወጣ በተሳታፊዎች መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡
በፍትሕ ሚኒስቴር በሕግ ጉዳዮች የአለምአቀፍ ትብብር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ የሱፍ ጀማው መድረኩን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ ስምምነቶቹን መሠረት አድርገው ለሚያዘጋጁ አህጉር አቀፍ ሪፖርቶች የዚህ አይነቱ የውይይት መድረክ መካሄዱ በመረጃ ጥንቅሩ የተሻለ እና የተሟላ ሪፖርት ለማዘጋጀት የበኩሉን ሚና ይጫወታል ብለዋል።
የውይይት መድረኩ የፍትሕ ሚኒስቴር እና የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ትብብር የተዘጋጀ ሲሆን የአውሮፓ ህብረት ለመድረኩ እውን መሆን የበኩሉን አበርክቷል፡፡