የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የመንግሥት ሕግና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ በላይሁን ይርጋ ከዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት የኢትዮጵያ ቢሮ የፍልሰት ተጎጂዎች ድጋፍ ከፍተኛ ኃላፊ ሳራ ባሻ ጋር በጽ/ቤታቸው ተወያይተዋል፡፡
ክቡር አቶ በላይሁን በውይይቱ ወቅት እንደተናገሩት፤ ዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት የኢትዮጵያ የፍልሰት አስተዳደር ሥርዓት እንዲጠናከር በተለይም በሕግና በፖሊሲ፣ በአደረጃጀትና በተቋማት አቅም ግንባታ እንዲሁም በፍልሰት ተጎጂዎች ድጋፍና መልሶ ማቋቋም ሂደት ሁለንተናዊና ተኪ የለሽ ሚና በመወጣት ላይ ይገኛል፡፡
ፍትሕ ሚኒስቴር በፍልሰት አስተዳደር ውስጥ እንደ ትብብር ጥምረት ሰብሳቢነቱ እንዲሁም እንደ አንድ ተዋናይ ከዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት ጋር የሚያከናውናቸው የትብብር ሥራዎች በይበልጥ እንደሚጠናከሩ ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡
እንደ ክቡር አቶ በላይሁን ገለጻ በቅርቡ የጸደቀው የነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ስትራቴጂ በሥራ ላይ እንዲውል ከድርጅቱ ጋር በቅርበት የሚሰራ ይሆናል፡፡
የፍትሕ ሚኒስቴር የትግራይ ክልልን ጨምሮ በደቡብ፣ በመካከለኛውና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች የፍልሰት የትብብር ጥምረት ለማደራጀት የያዘው ዕቅድ እንዲሳካ ከዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት ጋር በትብብር እንደሚሰራም ክቡር ሚኒስትር ዴዔታው ተናግረዋል፡፡
ረቂቅ የፍልሰት ፖሊሲው እንዲጸድቅ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ክትትሉን አጠናክሮ ይቀጥላል ያሉት ክቡር አቶ በላይሁን፤ በረቂቅ ደረጃ የሚገኘው የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ድጋፍና ጥበቃ የሕግ ማዕቀፍ ተጠናቅቆ እንዲቀርብም ይደረጋል ብለዋል፡፡
የዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት የኢትዮጵያ ቢሮ የፍልሰት ተጎጂዎች ድጋፍ ከፍተኛ ኃላፊ ሳራ ባሻ በበኩላቸው ድርጅታቸው ከፍትሕ ሚኒስቴር ጋር የሚያደርገው ትብብርና አጋርነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ መምጣቱን ገልጸው፤ በቅርቡ በሁለቱ ተቋማት መካከል የተፈረመው የትብብር ሥምምነትም ለዚሁ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሥምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግም የሁለቱ ተቋማት የጋራ ስትራቴጂክ ዕቅድ ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል፡፡
ብሔራዊ የፍልሰት ምክር በስትራቴጂክ ጉዳዮች ላይ አቅጣጫ እንዲያስቀምጥ ለማድረግ ዓመታዊ ስብሰባውን እንዲጠራ የፍትሕ ሚኒስቴር ሚና ወሳኝ መሆኑን የገለጹት ኃላፊዋ፤ የምክር ቤቱን መድረክም የፍልሰት ፖሊሲው በመንግሥት በኩል ቅድሚያ ተሰጥቶት እንዲጸድቅ ለማሳሰብ ዓይነተኛ አጋጣሚ ማድረግ እንደሚቻልም አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡
እንደ ወ/ሮ ሳራ ገለጻ የትግራይ ክልልን ጨምሮ በሌሎችም የትብብር ጥምረት ባልተደራጀባቸው ክልሎች አደረጃጀቱን ለመዘርጋት ድርጅታቸው ድጋፍ የሚያደረግ ሲሆን፤ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ድጋፍና ጥበቃ የሕግ ማዕቀፍ ከጸደቀ በኋላ ተግባራዊ ለማድረግ እንዲሁም የሕግ ማስከበርና ወንጀል መከላከልን አቅም ከማጎልበት እና ከሱዳን ተመላሽ ተጎጂ ፍልሰተኞችን የመደገፍ ሥራዎችንም ድርጅታቸው ተቀዳሚ አጀንዳ አድርጎ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡