በፍልሰት ምርምር ላይ ያተኮረ አገራዊ የምክክር መድረክ ተካሄደ

National Consultation Forum Held on Migration Research

በፍትሕ ሚኒስቴር የብሔራዊ ትብብር ጥምረት ጽ/ቤት ከኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴር እና ከጂ አይ ዜድ ጋር በመተባበር በፍልሰት ምርምር ላይ ትኩረት ያደረገ አገራዊ የምክክር መድረክ ታህሳስ 10 ቀን 2016 ዓ.ም በኢሊሌ ሆቴል አካሂዷል፡፡

በምክክር መድረኩ የፍልሰት ትብብር ጥምረት አባል ተቋማት ተወካዮች ፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመራማሪዎች እና ምሁራን ፣ የዓለም ዓቀፍ ተቋማት እና ኤምባሲ ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡

የብሔራዊ ትብብር ጥምረት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አብርሃም አያሌው የፍልሰት አስተዳደር ጉዳይ የመንግሥት አይነተኛ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ጠቁመው ዜጎቻችን ህገ ወጥ በሆነው የፍልሰት መስመር መተላለፊያ እና መዳረሻ ሃገራት ከፍተኛ የሆነ የመብት ጥሰት እና ሞት እየደረሰባቸው በመሆኑ መደበኛ ያልሆነውን ፍልሰት ከመከላከል ባሻገር መደበኛ የሆነውን ፍልሰት ለማበረታታት እና የሰዎችን ህጋዊ እንቅስቃሴ የተሳካ ለማድረግ እንዲሁም ህጋዊ የሆነ የውጪ አገር የሥራ ስምሪት እንዲስፋፋ ለማድረግ መሰረተ ሰፊ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ኃላፊው አያይዘውም በሀገራችን ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለውን ግፍ ለመከላከል በሌላ በኩል ደግሞ ከፍልሰት የሚገኘውን ጥቅም አሟጠን ለመጠቀም እንዲመች በአዋጅ እና በመመሪያ ከተቋቋሙት 6 የስራ ቡድኖች ውስጥ የፍልሰት ምርምር የስራ ቡድን አንዱ መሆኑን በመጠቆም ለአገሪቱ የፍልሰት ጉዳዮች በፖሊሲ፣ በሕግ፣ በስትራቴጂ እና በፕሮግራም የተደገፈ ሁሉን አቀፍ ሳይንሳዊ ምላሽ ለመስጠት እንዲቻል ውጤታማ የፍልሰት ምርምር ስራዎችን ማካሄድ የፍልሰት ምርምር የስራ ቡድን የተቋቋመበት ዓላማ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ይህ የምክክር መድረክ በትብብር ጥምረቱ የምርምር የስራ ቡድን አባል ተቋማት ተወካዮችን ፣ ዩኒቨርሲቲዎችን ፣ የምርምር ማዕከላትንና ሀገር በቀል እና ዓለም አቀፍ አጋሮችን በአንድነት በማሰባሰብ ስለ ፍልሰት ምርምር ጉዳዮች ለመምከር ያለመ መሆኑን አውስተዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲዎች እና የምርምር ተቋማት በሀገሪቱ ቀዳሚ ፍላጎት ላይ የተመሰረቱ ምርምሮችን በማካሄድ ለመንግሥት የፖሊሲ፣ የሕግ እና የውሳኔዎች መነሻ የሚሆኑ ሳይንሳዊ የመፍትሄ ሃሳቦችን ሊያመነጩ እንደሚገባ የገለፁት ደግሞ በኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ የተከበሩ አቶ ኮራ ጡሸኔ ናቸው፡፡ እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለፃ ተቋማቸው የምርምር ማዕከላት እና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በፍልሰት ዙሪያ ምርምር እንዲያካሂዱ የማስተባበር ስራን ያከናውናል፡፡ ሚኒስቴር መስሪያ ቤታችን ከጥምረት ፅ/ቤቱ ጋር በመተባበር የፍልሰት ምርምር የስራ ቡድን የሚመራበትን አገራዊ ሰነድ (Migration Research Thematic Working Group Guiding Document) ረቂቅ አዘጋጅቷል ሲሉ አቶ ኮራ አክለው ገልፀዋል፡፡

ሚኒስትር ድኤታው በዚህ የምክክር መድረክ በጥምረቱ ማዕቀፍ ለታቀዱ ተግባራት አፈፃፀም ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ የሚያግዙ ጠቃሚ ሃሳቦች የሚነሱበት እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡

በመድረኩ የኢትዮጵያ የፍልሰት አስተዳደር የሕግና የአደረጃጀት ማዕቀፎች ፣ በብሔራዊ የፍልሰት ትብብር ጥምረት የፍልሰት ምርመራ ቡድን አመታዊ እቅድ ፣ የፍልሰት ምርምር የስራ ቡድን የሚመራበትን ሀገራዊ ሰነድ ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

ሃገራዊ የምክክር መድረኩ በፍትሕ ሚኒስቴር የብሔራዊ ትብብር ጥምረት ጽ/ቤት ፣ ትምህርት ሚኒስቴር እና ጂ አይ ዜድ በጋራ የተዘጋጀ ሲሆን ከተሳታፊዎች በርካታ እና ጠቀሜታቸው የጎላ ግብአቶችን መሰብሰብ እንደተቻለ ተገልጿል፡፡

Tagged Under: act Consultation decree Forum Human Trafficking Illegal Migration law legislation Migration Migration Management Migration Research ministry ministry of education National national consultation forum National Strategy Policy proclamation program regular migration Regulation Research scientific research Stakeholder Consultation statute Strategy
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች