የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር ብሔራዊ የፍልሰት ትብብር ጥምረት ጽ/ቤት፣ ከሲቪኤም እና ፍሪደም ፈንድ ጋር በመተባበር የተዘጋጀ በሰው የመነገድና ሰውን በህገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀሎች ዙሪያ ባለፉት 6 ወራት በፌደራል እና ክልሎች ደረጃ የተከናወኑ ተግባራት አፈፃፀም ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል የተከበሩ አቶ ለማ ተሰማን ጨምሮ የተቋማችን ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች፣ የተለያዩ ተቋማት ተወካዮች እንዲሁም ከክልል ፍትሕ ቢሮዎች የተወከሉ አካላት በተገኙበት የተካሄደውን የውይይት መድረክ በንግግር የከፈቱት በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐ/ሕግ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ተስፋዬ ዳባ ሲሆኑ፤ በህገ-ወጥ መንገድ ሰዎችን ድንበር የማሻገርና በሰዎች የመነገድ ወንጀሎችን ለመከላከል በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ገልፀው በዚህም ረገድ በህገ-ወጥ ፍልሰት ላይ ግንዛቤ የመስጠት፣ በህገ-ወጥ መንገድ ድንበር የሚሻገሩ ዜጎችን በመመለስ እንዲቋቋሙ ድጋፍ የማመቻቸት ስራ፣ ወንጀል የመከላከል ተግባርን ከክልሎችና ጎረቤት ሀገራት ጋር በትብብርና በቅንጅት መሥራት፣ በሥልጠና የፍትሕ አካላትን አቅም መገንባት፣ እንዲሁም በወንጀል ፈፃሚዎች ላይ አስፈላጊውን ምርመራ በማድረግ ክስ መስርቶ እስከ 25 ዓመት የሚደርስ የእስራት ቅጣት እንዲወሰንባቸው የማድረግ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው አያይዘውም በሰው የመነገድና በህገ-ወጥ መንገድ ሰውን ድንበር ማሻገር ወንጀሎች ዙሪያ በቂ ትብብርና ቅንጅት አለመጠናከር፣ የምርመራ ጥራት ጉድለት፣ የወንጀል ተጎጂዎች ሰብዓዊ መብታቸው ተከብሮ ምርመራ የሚደረግበትን ሁኔታ በሚፈለገው ደረጃ አለመሟላት እና ተያያዥ ጉዳዮች አሁንም የሚታዩ ክፍተቶች መሆናቸውን አስታውሰው፤ የውይይት መድረኩ የልምድ ልውውጥ የሚደረግበት፤ የትብብርና ቅንጅት፣ መረጃ የመቀባበል ሂደቶች ያሉበትን ደረጃ የሚቃኝበት በመሆኑ በንቃት ተሳትፎ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳሰበዋል፡፡
በመቀጠልም በመድረኩ በሰው የመነገድና ሰውን በህገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀሎች ዙሪያ በፌደራል ደረጃ የተከናወኑ ተግባራትን አስመልክቶ የ 6 ወራት ሪፖርት ያቀረቡት በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐ/ሕግ ዘርፍ የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ዳሬክቶሬት ጄኔራል ዳሬክተር አቶ ዮሲያድ አበጀ ሲሆኑ፣ በሪፖርቱ እንደተመላከተው በእነዚህ ወንጀሎች ላይ ቅድመ ጥቆማ ምርመራ (Proactive Investigation) ለማድረግ መረጃ የማጠናከር ስራ እየተሰራ እንደሚገኝና ከጎረቤት ሀገራት ጋር ጭምር በትብብር ስምምነት በመፈራረም የመከላከል ተግባሩ በመከናወን ላይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ምስክር እና ተከሳሽ ባለመቅረብ ምክንያት መዛግት መቋረጥ በአፈጻጸም ወቅት ከታዩ ችግሮች መካከል እንደነበሩ አንስተው ክስ በቀረበባቸው ተከሳሾች ላይ እስከ 25 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ መደረጉን አንስተዋል፡፡
በሌላ በኩል በሰው የመነገድና ሰውን በህገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀሎችን በመከላከል ረገድ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት፣ ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እና ሌሎች ከሚመለከታቸው ተቋማት የሕግ ማስከበር ቡድን በ 6 ወራት ያከናወናቸውን ተግባራት በሚመለከት በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ብሔራዊ የትብብር ጥምረት ጽ/ቤት ቡድን መሪ በሆኑት አቶ አቤል ገ/እግዚአብሔር አማካኝነት ቀርቧል፡፡ በተጨማሪም የድሬደዋ ከተማ አሰተዳደር፣ የሶማሌ፣ ትግራይ እና አማራ ክልል የፍትሕ ቢሮ ተወካዮች አማካኝነት የ6 ወር አፈጻጸማቸው በዝርዝር ቀርቧል፡፡
በመጨረሻም በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐ/ሕግ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ተስፋዬ ዳባ እና የመንግሥት ሕግ እና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ በላይሁን ይርጋ አወያይነት በቀረቡት ሪፖርቶች ላይ ዝርዝር ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን፤ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጋራ ለመሥራት ሁኔታውን ከስር መሰረቱ ማጤንና በቅንጀት በኩል የሚታዩ ክፍተቶችን ማጠናከርና ችግሩን ቢያንስ በተወሰነ ደረጃ ለመግታትና ለመከላከል ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ የተገለፀ ሲሆን፤ በፌደራል መንግሥት በኩል ከጎረቤት ሀገራት ጋር ግንኙነት የማድረግ የመነጋገር ስራ እየተሰራ መሆኑን በማውሳት፤ በተመሳሳይ በተለይም በሀገር ውስጥ የህገወጥ ፍልሰት መነሻና መድረሻ እንዲሁም መተላለፊያ ሆነው የሚገኙ ክልሎች እርስ በርስ ተገናኝተው ቅንጅት በመፍጠር ያላቸውን አቅም ተጠቅመው ሊሰሩ እንደሚገባ ተመላክቷል፡፡