የፍትሕ ሚኒስቴር ለሀገሪቱ የፍትህ ሥርዓት መጠናከርና ለሕግ የበላይነት መስፈን ታሪካዊ ፋይዳ አለው የተባለው አዲሱ የወንጀል ሥነ-ሥርዓትና የማስረጃ ሕግ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጋቢት 24 ቀን 2018 ዓ.ም መጽደቁን በማስመልከት በረቂቅ ዝግጅት ሂደቱ ላይ ጉልህ አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላት ሚያዚያ 22 ቀን 2018 ዓ.ም የእውቅና መርሃ-ግብር አካሂዷል።
ይህ አዲስ ሕግ ከ1954 ዓ.ም ጀምሮ ለ6 አስርተ አመታት ዓመታት ያህል ሲያገለግል የነበረውንና የዘመኑን የሕግ ፍላጎት የማይመጥነውን ነባር የስነ ሥርዓት ህግ በመተካት በፍትሕ አሰጣጥ ሂደት ላይ መሠረታዊ ለውጦችን ይዞ መጥቷል።
ከነዚህም ውስጥ አንዱ የማስረጃ ሕግ መካተት ሲሆን ፤ እስካሁን የነበረውን ወጥ የሆነ የማስረጃ ሕግ አለመኖር ክፍተት በመሙላት በማስረጃ አቀባበልና ምዘና ላይ ግልጽነትና መተንበይ የሚቻል አሰራር እንዲሰፍን ያደርጋል።
ሌላኛው የጥፋተኝነት ድርድር (Plea Bargaining) ሥርዓትን በሕግ ዕውቅና በመስጠት የፍርድ ቤቶችን እና የፍትሕ አካላትን የሥራ ጫና ከመቀነሱም በላይ የሀገርን ሀብትና ጊዜ የሚታደግ አሰራር ዘርግቷል።
በተጨማሪም ሕጉ የሰብአዊ መብቶችና የተጎጂዎች ጥበቃን በተመለከተ በተጠርጣሪዎች ላይ ሊፈጸሙ የሚችሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ከመከላከል ባለፈ፣ ለምስክሮችና ለወንጀል ተጎጂዎች ልዩ ጥበቃና ትኩረት የሚሰጡ ድንጋጌዎችን አካቷል።
ከዚህም ጋር ተያይዞ ሕጉ እስካሁን በአፈጻጸም ወቅት ይታዩ የነበሩ ክፍተቶችን የሚሞላ እና የወንጀል ፍትሕ አስተዳደሩን በብዙ መልኩ ወደፊት ሊያሰኬድ የሚችል ከመሆኑም በላይ ለፍትሕ ሪፎርሙ ስኬት ትልቅ ምዕራፍ እንደሆነ የተወሳ ሲሆን፤ በቀጣይም ሕጉን በተሟላ ሁኔታ ተግባራዊ ለማድረግና ለባለሙያዎች ግንዛቤ ለመፍጠር የሁሉል ባለድርሻ አካላት ርብርብ አስፈላጊ እነደሆነ በመድረኩ ተጠቁሟል፡፡
በመጨረሻም ሕጉን በማርቀቅ፤ሙያዊ ድጋፍ ሲያደርጉ ለቆዩ የሕግ ባለሙያዎች፣ የሥራ ኃላፊዎችና አጋር አካላት ላቅ ያለ ምስጋና በማቅረብና ዕዉቅና በመስጠት መርሃ-ግብሩ ተጠናቋል፡፡