የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ከሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ተግባራዊ እያደረገ ያለዉን በአገር ዓቀፍ ደረጃ በሴቶች እና ሕፃናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን መረጃ ለመመዝገብ የሚያስችለዉን ሲስተም ተግባራዊነቱን ይበልጥ ለማጠናከር አጋዥ የሚሆኑ የተለያዩ የቴክኖሎጂ ቁሳቁሶች ድጋፍ ከ.ዩ.ኤን.ውሜን(UN-WOMEN) በኩል ሚያዝያ 6/2028 ዓ.ም ተደርጎለታል፡፡
የተደረገዉ የቁሳቁስ ድጋፍ በተለይም ሲስተሙን ተግባራዊ ለማድረግ በሙከራነት በፌዴራልና በክልል ደረጃ እየተተገበረ ላለዉ ስራ የሚኖረዉ ሚና ከፍተኛ መሆኑ የተጠቆመ ሲሆን፣ ሲስተሙ በአገር አቀፍ ብሎም በክልል ደረጃ የሚያበረክተዉ አስተዋፅኦ የጎላ መሆኑ ተገልጿል።
በሴቶች እና ሕፃናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች መረጃ በተሟላ ሁኔታ መያዙ ቀጣይነት ላለዉ ዕቅድ፣ለበጀት እና ለፖሊሲ አዉጭዎች የሚኖረዉ ጠቀሜታ ትልቅ በመሆኑ፣ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች ሲስተሙን ተግባራዊ ከማድረግ ጋር ተያይዞ የሚያስፈልገዉ ቁሳቁስም ሰፊ እንደሆነና ይህንኑ ለማሳካትም በቀጣይ ጉዳዩ ከሚመለከታቸዉ ባለድርሻ አካላት ጋር በተጠናከረና በተናበበ መልኩ በጋራ መስራት እንደሚገባ ተጠቁሟል።
በዛሬዉ ዕለት በዩ.ኤን.ውሜን በኩል ግምታቸው ስምንት ሚሊዮን ብር የሆነ ዴስክ ቶፖች፣ ላፕቶፕ ኮምፒውተሮች፣ ስካነር፣ የድምፅ ሪከርደር፣ የፎቶ ካሜራ እና ሲግኒችር ፓዶች ድጋፍ የተደረገ ሲሆን ትብብሩ በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገልጿል።
ርክክቡ የፍትሕ ሚኒስቴር የተቋም ግንባታና ሪፎርም ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ኤርምያስ የማነብርሃን (ዶ/ር) እና የዩ.ኤን.ውሜን ኢትዮጵያ ተወካይ ሚስ ጃኔት ኪም በተገኙበት ተካሂዷል።