የፍትሕ ሚኒስቴር የመንግሥት የሕግና ፍትሕ አገልግሎት ሚኒስትር ዲኤታ ክቡር አቶ በላይሁን ይርጋ ይህን ያሉት የአስተዳደር ስነ -ሥርዓት ሕግ ለሕግ የበላይነትና ለመልካም አስተዳደር ግንባታ በሚል መሪ ቃል በአፋር ብሔራዊ ክልልላዊ መንግሥት ሰመራ ከተማ እየተካሄደ ባለው የጋራ ምክክር መድረክ ላይ ተገኝተው ለተሳትፊዎች ባስተላለፉት መልእክት ነው።
የአገራችን ሕዝብ በፍትሕ ስርአቱ ላይ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ በተለይም አስፈፃሚ አካላት ከሚሰጧቸው አገልግሎቶች ጋር ተያይዞ ከመመሪያ አወጣጥና አተገባበር ጋር የሚገናኙ ቅሬታዎች እንደሚነሱ የጠቆሙት ክቡር ሚኒስትር ዲኤታው እነዚህ የፍትሕ ጥያቄዎችም በአጠቃላይ በአስተዳደራዊ ፍትሕ ቅኝት ውስጥ የሚታዩና በአስተዳደር ስነ ሥርዓት ህጉ የሚመሩ መሆናቸውን አክለዋል።
በሕግ የመዳኘት መብት፣የዜጎችን መብት ማረጋገጥና በዜጎችና በመንግሥት አካላት የመረጃ ልውውጥ እንዲኖር ማድረግ የሚሉ ዓላማዎችን የያዘው የአስተዳደር ስነ ሥርዓት ህጉ፣ ዜጎች በአሠራር ሂደቶች ላይ ምርጫቸውን እንዲያንፀባርቁና መንግሥትም የተሻሉ ዘዴዎችን ለማፈላለግ መረጃ እንዲሰበሰብና ጥናት እንዲያደርግ የሚያስቻል አሠራርን የሚዘረጋ በመሆኑ ህጉ እጅጉን አስፈላጊ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
በመሆኑም ሁሉም ክልሎች ይህንን ሕግ አውጥተው ተግባራዊ ካላደረጉ መልካም አስተዳደር እና የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ እንደማይቻል በመገንዘብ ህጉን ያላወጡ ክልሎች በተያዘው በጀት ዓመት ህጉን አውጥተው እንዲተገብሩ ሚኒስትር ዲኤታው አሳስበዋል።
የአፋር ክልል ፕሬዝዳንት ተወካይ አቶ አሊ መሀመድ በበኩላቸው የጋራ ምክክር መድረኩ በተለይም የፌደራልና የክልል ተቋማት ዕርስ በርስ ልምዳቸውን በመለዋወጥና የተግባርና የአንድነት ቅንጅት በመፍጠር አሰራሮቻቸውን ወጥ ለማድረግ እንደሚያግዝ ገልፀው ፍትሕ ሚኒስቴርም ክልላቸው ይህን ትልቅ አጀንዳ እንዲያዘጋጅ እድሉን ስለሰጣቸው ምስጋና አቅርበዋል።
ምክክሩ በጠዋቱ ቆይታዉ የአስተዳደር ስነ-ሰርአት ሕግ ለሕግ የበላይነት ያለው ፋይዳ በተለይም ፌዴራላዊ ሥርዓትን የሚከተሉ ሀገራት የአስተዳደር ስነ-ሥርዓት ሕግ አወጣጥና አተገባበር ምን እንደሚመስልና ከነዚህም ሀገራት መካከል ለኢትዮጵያ ትምህርት የሚሆኑ ጉዳዮች ምንድን ናቸው? የሚል ጽሑፍ በባለሙያዎች ቀርቦ በተሳታፊዎች ዉይይት የተደረገበት ሲሆን በከስአቱ ዉሎዉ ደግሞ በአስተዳደር ስነ ሥርዓት አተገባበር ሂደት የፍርድ ቤቶች ሚና የሀገራት ንፅፅር ቅኝት እንዲሁም በኢትዮጵያ ወደፊት ሊወሰዱ የሚገባቸውን አካሄዶች የተመለከተ ጽሑፍ ቀርቦ በተሳታፊዎች ዉይይት የሚደረግበት ይሆናል።
በመድረኩም ላይ የፍትሕ ሚኒስቴር የመንግሥት የሕግና ፍትሕ አገልግሎት ሚኒስትር ዲኤታ ክቡር አቶ በላይሁን ይርጋ ፣ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ክብርት ወ/ሮ ሌሊሴ ደሳለኝ ፣ በምክትል ፕሬዝዳንት ማዕረግ የአፋር ክልል የኢኮኖሚ ክላስተር አሰተባባሪ እና የፕሬዝዳቱ ተወካይ የሆኑት ክቡር አቶ አሊ መሃመድን ጨምሮ፣ የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንቶች፣ የክልል ፍትሕ ቢሮ ሃላፊዎች እንዲሁም የፍትሕ ሚኒስቴር መካከለኛ አመራሮች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡