በወንጀል ድርጊት የተገኘ ንብረት ወይም ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብንና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመቆጣጠርና ለመከላከል የወጣው አዋጅ ቁጥር 780/2005 ‘ን ለማሻሻል የወጣውና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀው አዋጅ ቁጥር 1387/2017ን አስመልክተ የተለያዩ የመንግሥት እና መንግስታዊ ያልሆኑ የሚዲያ አካላት በተገኙበት ሰኔ 12 ቀን 2017 ዓ.ም በፍትሕ ሚኒስቴር ዋናው መስሪያ ቤት አዳራሽ ጋዜጣዊ ጉባዔ ተካሂዷል፡፡
በዚህም ወቅት አዋጅ ቁጥር 780/2005 በወንጀል የተገኘን ንብረት ወይም ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብን እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የሚያስችሉ በርካታ ድንጋጌዎችን ይዞ የነበረ ቢሆንም ወቅቱን ያገናዘበ እና በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ካለው አሠራር ጋር በተጣጣመ ደረጃ ሥራውን ውጤታማ አድርጎ ለመምራት በሚያስችል አግባብ ለመምራት የተወሰኑ ክፍተቶች በመኖራቸው ፤ በወንጀል ተግባር የተገኘ ገንዘብን ወይም ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ የማቅረብ እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳት ወንጀል ድንበር ተሻጋሪና ዓለም አቀፋዊ ችግር በመሆኑ ወቅቱን የጠበቀ ጠንካራ ሕግና አሠራር በመዘርጋት የተረጋጋ፣ ግልፅነት ያለው፣ ጤናማ እና ቀልጣፋ የፋይናንስ ሥርዓት የሚያስፈልግ በመሆኑ፤ የተለያዩ የፋይናንስ እና ፋይናንስ ነክ ያልሆኑ ተቋማት ትክክለኛነትና ተጠቃሚ ባለሀብቶች እነማን እንደሆኑ ለመለየት እንዲሁም ወንጀልን ለመከላከል በሚያስችል መልኩ መረጃዎችን ለመያዝ የሚያግዝ አሠራር ማስቀመጥ በማስፈለጉ፤ ከፋይናንስ ግብረ ኃይሉ ምክረ-ሀሳብ እና ዘርፉን በተመለከተ ባለፉት 12 ዓመታት ሀገራችን ፈርማ ከተቀበለቻቸው ሥምምነቶች ጋር የተጣጣመ እንዲሆንና በተግባር ያጋጥሙ ክፍተቶችን ለመሙላት እንዲቻል የሕግ ማዕቀፉን ማሻሻል አስፈላጊ እንዲሆን ካደረጉት ምክንያች ዋነኞቹ እንደሆኑ ተጠቁሟል፡፡ በዚህም መሠረት አዋጅ ቁጥር 1387/2017 በአዋጅ ቁጥር 780/2005 ውስጥ ካሉት 58 አንቀፆች 14ቱ ላይ ማሻሻያ በማድረግ የነበሩ ክፍተቶችን መሙላት የሚያስችል እንደሆነ ተገልጿል፡፡
በአዋጅ ቁጥር 780/2005 ላይ በተለይም አመንጪ ወንጀሎች በግልፅ ካለመቀመጣቸው ጋር ተያይዞ ይፈጠር የነበረውን ችግር ለመቅረፍ በማሻሻያ አዋጁ ላይ ግልጽ ትርጉም ከመስጠት ጀምሮ 21 አመንጪ ወንጀሎች በዝርዝር በአባሪነት እንዲካተቱ ተደርገዋል፤ ወንጀሉን ለመከላከል የሚስያችል ጠንካራ የአሰራ ስርዓት አስፈላጊ በመሆኑ አዋጁ በተለይም ከሱፐርቪዝን(Risk Based Supervision) ጋር በተያዘዘ አስቻይ ሁኔታዎችን በግልፅ አስቀምጧል፤ ጥሬ ገንዘብን ከማጓጓዝ ጋር በተያያዘ አዋጁ ግልፅ ያልሆኑ ጉዳዮች የነበሩት ሲሆን አሁን ግን የንግድ እንቅስቃሴን በማይጎዳ መልኩ እንዲፈፀም ተደንግጓል፤ በሕግ ሰውነት የተሰጣቸው አካላትን በተመለከተም በተለይም ዋና ተጠቃሚዎች እነማን እንደሆኑ መለየት የሚያስችል ሁኔታ እንዲካተት ተደርጓል፤
በሽፋን ስር የሚደረጉ ምርመራዎችን ጨምሮ ሌሎች ልዩ የምርመራ ስልቶች የሚተገበሩበትን ሁኔታ ከሕገ መንግስቱ እና ሀገራችን ከተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ስምምነቶች ጋር በተጣጣመ አግባብ በግልጽ ማስቀመጥ እጅጉን በማስፈለጉ ማሻሻያው ይህን እንዲያካትት መደረጉ የተገለጸ ሲሆን ከዚህ አንጻር ልዩ የምርመራ ዘዴዎች በተለይም በሽፋን ስር የሚደረግ ምርመራ ምንነትና አስፈላጊነት እንዲሁም ወንጀል መርማሪዎች ምርመራውን ለማከናወን ተልእኮ ተቀብለው ስራቸውን በሚሰሩበት ጊዜ ተገደውና ያለፍላጎታቸው ወንጀሉን ከሚፈጽሙ ሰዎች ጋር ዋና ወንጀል አድራጊ ሆነው በሚገኙበት ጊዜ የሚኖራቸውን የሕግ ከለላ (Legal immunity) በተመለከተ በግልፅ መቀመጥ መቻል የሚሉ የተሸሻሉ ጉዳዮች ላይ ሰፋ ያሉ ማብራሪያዎች ተሰጥተዋል፡፡
በማብራሪያውም በተለይ ዓለም በዘመን አመጣሽ ሥልጣኔዎችና ቴክኖሎጂዎች እያደገችና እየተሳሰረች በምትሄድበት ጊዜ የወንጀል አፈፃፀም ዘዴዎችም እጅግ በጣም በረቀቀና በተወሳሰበ ሁኔታ ዓለም አቀፍ ባህሪ በመላበስ እንደሚፈጸሙ፣ ወንጀሎች በአፈፃፀማቸውና በባህሪያቸው በሕብረተሰቡ፣ በዜጎችና በመንግሥት ላይ የሚፈጥሩት ስጋትና የሚያስከትሉት ውጤትም እንደሚለያይ፣ በረቀቀ የአፈፃፀም ስልትና ዘዴ ዓለም አቀፋዊ ባህሪ ያላቸው፣ ከፍተኛ ማሕበረሰባዊ ጉዳት የሚያስከትሉ እጅግ በጣም የተወሳሰቡና ከባባድ ወንጀሎች ሲፈፀሙ በመደበኛ የምርመራ ስልትና ዘዴ ወንጀለኞችን መመርመር፤ መያዝ፣ ክስ መመስረትና ማስቀጣት እንደማይቻል እና ከዚህ አንጻር ከመደበኛ የምርመራ ስልቶች ባሻገር ልዩ የምርመራ ዘዴዎችን ተግባራዊ ማድረግ እጅግ አስፈላጊ እንደሚሆን ተወስቷል።
እነዚህ ልዩ የምርመራ ስልቶች በማስገደድ ማስረጃ ከመሰብሰብና ምርመራ ከማከናወን ተግባር ፍጹም የተለየ ጽንሰ-ሐሳባዊና ሕጋዊ ልዩነት ያላቸው መሆናቸውን፣ በማስገደድ ማስረጃን መሰብሰብ ወይም ምርመራ ማከናወን ኢ- ሕገ መንግሥታዊ ከመሆኑ በተጨማሪ የወንጀል፣ የፍትሐብሔርና አስተዳደራዊ ተጠያቂነት የሚያስከትል ሕገ ወጥ ተግባር መሆኑን፣ ከዚህ አኳያ በሽፋን ስር የሚደረግ ምርመራ መርማሪዎች በድብቅ፣ ማንነታቸውን በመቀየር ወይም ተጠርጣሪዎች ጋር ተመሳስለው በመቅረብና በመቀላቀል ወንጀል ፈጻሚዎችንና የወንጀል ፍሬዎችን መከታተልና ማስረጃዎችን ማሰባሰብ የሚችሉባቸው የምርመራ ስልቶች እንጂ በማስገደድ ማስረጃ የሚሰባሰብባቸው መንገዶች አለመሆናቸውን መገንዘብ እንደሚያስፈልግ በአጽንኦት ተገልጿል፡፡ በተያያዘም እነዚህ የምርመራ ስልቶች በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸረ-ሙስና ስምምነት (አንቀጽ 50)፣ በተባበሩት መንግሥታት ጸረ-ድንበር ተሻጋሪና የተደራጁ ወንጀሎች ስምምነት (አንቀጽ 20) እንዲሁም በሌሎች ዓለም አቀፍ ስምምነቶች እውቅና የተሰጣቸው የምርመራ ሥልቶች ሲሆኑ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ሕግጋት እና የፖሊሲ ማዕቀፍ አንጻርም በወንጀል ፍትሕ ፖሊሲው፣ በነባሩ አዋጅ ቁጥር 780/2005፣ በንብረት ማስመለስ አዋጅ ቁጥር 1364/2017 እንዲሁም በአዋጅ ቁጥር 1176/2012784 ላይ እውቅና የተሰጣቸው ናቸው ተብሏል።
ከዚህ አኳያ ማሻሻያ አዋጁ ፍርድ ቤት በሽፋን ስር የሚደረግ ምርመራን ተግባራዊ እንዲያደርግ አሳማኝ ምክንያት ሊፈቅድለት እንደሚችል፣ ሲፈቅድለትም ምርመራው የሚፈጸምበትን ዘዴ፣ የአተገባበር ሁኔታ፣ የሚከናወንበትን ጊዜ በትዕዛዙ ላይ በግልጽ ማስቀመጥ እንዳለበት ደንግጓል። ሆኖም ግን መርማሪው ፍርድ ቤት አሳማኝ ምክንያት ሲፈቅድለት በሽፋን ስር የሚደረግ ልዩ የምርመራ ዘዴን ይተገብራል ሲባል በተጠርጣሪዎች ወይም በሌላ ሦስተኛ ወገኖች ላይ ወንጀል ሊፈጽምባቸው ይችላል፤ ወንጀሉን ከፈጸመባቸው በኋላም በወንጀል አይጠየቅም የሚል ሳይሆን ከተጠርጣሪዎች ጋር የወንጀል ተካፋይ ወይም ግብረ-አበር በመሆን በራሱ ፈቃድ አስቦና ፈቅዶ ሳይሆን ያለፈቃዱ፣ ተገዶ፣ በተጽእኖ፣ ወይም በተጠርጣሪዎች ሕገ ወጥ ትእዛዝ ወይም ከአቅሙ በላይ በሆነ ማንኛውንም ምክንያት ሌላ ከባድ ጉዳትን ለማስቀረት ወይም የተሰጠውን ሕጋዊ ተልእኮ ለማሳካት ሲል ወንጀል የሚፈጽምበት ሁኔታ ሲኖር ከወንጀል ክስ ነጻ የሚደረግበትን ሁኔታ ለማመላከት የተደነገገ ድንጋጌ መሆኑን መገንዘብ እንደሚያስፈልግ በጋዜጣዊ ጉባኤው ላይ በዝርዝር ተብራርቷል።
በመጨረሻም በጋዜጣዊ ጉባኤው ማብራሪያ በተሰጠባቸው ጉዳዮች ላይ ከሚዲያ አካት ለቀረቡ ጥያቄዎች በፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ክቡር አቶ ሙሉቀን አማረ እንዲሁም በፍትሕ ሚኒስቴር የሕግ ማርቀቅና ማጠቃለል ዳይሬክቶሬት ጀነራል፤ ዳይሬክተር ጀነራል አቶ አዲስ ጌትነት ሰፋ ያለ ምላሽ እና ማብራያ ተስጥቷል፡፡