በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የሰብዓዊ መብቶች ዳሬክቶሬት የፌደራል ባለድርሻ ተቋማትን በማስተባበር በተዘጋጀው 3ኛው ብሔራዊ የሠብዓዊ መብቶች የድርጊት መርሐ-ግብር ረቂቅ ሰነድ ሁለተኛ ዙር የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረክ ከትግራይ፤ ከደቡብ ኢትዮጵያ፤ ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ፤ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፤ ከሲዳማ እና ከኦሮሚያ ክልሎች ከተወከሉና በየደረጃው ካሉ ፈፃሚ ተቋማት የሥራ ሃላፊዎች ጋር ከጥር 15-16/ 2018 ዓ.ም በአዳማ ከተማ ተካሂዷል፡፡
መድረኩ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች አጠባበቅን ለማሻሻል ሲተገበር የቆየው 2ኛው የብሔራዊ ሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሐ-ግብር የትግበራ ጊዜው መጠናቀቁን ተከትሎ ሀገራችን አሁን ካለችበት የፖለቲካ ፤ የኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ሁኔታዎች ጋር በተጣጣመ መልኩ 3ኛ ዙር የድርጊት መርሐ-ግብር ማዘጋጀትና ማፀደቅ አስፈላጊ በመሆኑ በ2018 ዓ.ም ተሻሽሎ በተዘጋጀው 3ኛው ብሔራዊ የሠብዓዊ መብቶች የድርጊት መርሐ- ግብር ረቂቅ ሰነድ ላይ ከባለድርሻ አካላት ሰነዱን ሊያዳብሩ የሚችሉ ግብዓቶችን ለማሰባሰብ ታስቦ የተዘጋጀ ነው፡፡
3ኛው ብሔራዊ የሠብዓዊ መብቶች የድርጊት መርሐ- ግብር ረቂቅ ሰነድ በበርካታ ሂደቶች ውስጥ አልፎ የተዘጋጀ መሆኑ የተጠቆመ ሲሆን፤ የሰብዓዊ መብቶች የድርጊት መርሐ- ግብር በህገመንግስቱ የተቀመጡ መብቶችን ወደ መሬት የሚወርዱበት ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተቀበልናቸው ግዴታዎች በተለይ ሰብዓዊ መብት ላይ ትኩረት በማድረግ ወደ ተግባር የሚቀየሩበት በአጠቃላይ ከፍትሕ ዘርፉ ውጪ ያሉ ሌሎች አካላትም ሰብዓዊ መብትን ለማክበርና ለማስከበር እንዲሁም ለመተግበር የሚጠቀሙበት መሳሪያ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
በመድረኩ ብሔራዊ የሠብዓዊ መብት የድርጊት መርሐ- ግብር ምንነት ዓላማና መርሆዎች እንዲሁም ጠቀሜታ ፣ በኢትዮጲያ ብሔራዊ የሰብዓዊ ድርጊት መርሐ-ግብር የዝግጅት ሂደት ፣ ከ1ኛ እና 2ኛ ዙር መርሐ ግብሮች የተገኙ ልምዶች እና ዋና ዋና ዉጤቶች እንዲሁም የመርሃ ግብሩ ግብዓቶች እና የመርሐ-ግብሩን ይዘት አካቶ የያዘው 3ኛው ብሔራዊ የሠብዓዊ መብቶች የድርጊት መርሐ- ግብር ረቂቅ ሰነድ ቀረቧል፡፡
የረቂቅ የሰነዱን መቅረብ ተከትሎ ሰፊና ጥልቀት ያለው ውይይት በማካሄድ በርካታ ሰነዱ ለማዳበር የሚያግዙ ግብዓቶችን መሰብሰብ የተቻለ ሲሆን፤ በቀጣይ መሰል መድረኮች ከፌደራል እና ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች ጋር እንደሚካሄድ ታውቋል፡፡
የውይይት መድረኩ የፍትሕ ሚኒስቴር እና የአውሮፓ ሕብረት የወንጀል ፍትሕ አስተዳደሩን ለማሻሻል ባደረገው ድጋፍ የተዘጋጀ ነው፡፡