በሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና በብሔራዊ የፍልሰት ትብብር ጥምረት አማካኝነት በዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት ድጋፍ በደቡብ ክልል፣ ሐዲያ ዞን፣ ሆሳዕና ከተማ ታህሳስ 15 ቀን 2015 ዓ.ም. በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር መከላከል ላይ በማተኮር የተካሄደው የሕዝብ ንቅናቄ መድረክ ድህረ-ግምገማ በኢፌዴሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ተካሄደ፡፡
የመንግሥት ሕግና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው በመሩት በዚሁ የድህረ-ግምገማ መድረክ ላይ በዘርፉ ሥር የሚገኙ ሁሉንም የሥራ ክፍሎች የሚመሩ ዳይሬክተር ጀነራሎች፣ ዳይሬክተሮች፣ የጽ/ቤት ኃላፊዎች እንዲሁም የዘርፍ አማካሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
ክልል ርዕሰ መስተዳድርና የክልሉ የቢሮ ኃላፊዎች፣ የሐዲያ ዞን የየደረጃው አመራሮች እንዲሁም የአጎራባች ዞኖች የሥራ ኃላፊዎች፤ የዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት እና የሌሎች አጋሮች ተወካዮች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
በዚህ የሕዝብ ንቅናቄ መድረክ ድንበር ተሻጋሪ የሆነው የህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል በአገሪቱ ሕዝቦች ይልቁንም በሐዲያ ሕዝብ ላይ እያደረሰ ያለው አስከፊ ችግር በስፋት ተዳስሷል፡፡ በተጨማሪም ወንጀሉን በመከላከል ረገድ በተለይም ከግንዛቤ ፈጠራና ከሕዝብ ንቅናቄ አንጻር በተከናወኑ ተግባራት ዙሪያ በማህበረሰቡ ተወካዮች፣ በመንግሥት አካላት እና በአጋሮች ውይይት ተካሂዷል፡፡
ክቡር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ በመድረኩ ላይ ለተገኙት ሁሉም ተቋማት ኃላፊዎችና የየደረጃው አመራሮች ወንጀሉን በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ ሊያከናውኑ ስለሚገባቸው ሥራዎች ቀጣይ አቅጣጫዎችን በዝርዝር አስቀምጠዋል፡፡
በመድረኩ በውይይት ዳብረው የወጡት ሃሳቦችና ክቡር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስቀመጧቸው አቅጣጫዎችም “የሆሳዕና ሥምምነቶች” (Hosaena Declarations) ተብለው የተሰየሙ ሲሆን፤ በስምምነቱቹ መሠረትም በቀጣይነት በሃዲያና በከንባታ ጠንባሮ ዞኖች በሚገኙ ሁሉም ወረዳዎችና ቀበሌዎች ተመሳሳይ የሕዝብ ንቅናቄ መድረኮች የሚካሄዱ ይሆናል፡፡
ከእነዚህ የንቅናቄ መድረኮች የሚገኙት ልምዶችና እንዲቀመሩና ወደፊትም “መለወጥ በሀገር” በሚል መሪ ቃል በአማራ ክልል ወሎ አካባቢ እንዲሁም በኦሮሚያ ክልልም በተመረጡ አካባቢዎች ተመሳሳይ የሕዝብ ንቅናቄ መድረኮች እንዲደረጉ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡
የተሰጡትን አቅጣጫዎች ተግባራዊነት ለመከታተልም የኢፌዴሪ ሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የፍትሕ ሚኒስቴር፣ የስራና ክህሎት ሚኒስቴርና ሌሎች አካላት የተካተቱበት ኮሚቴ ክቡር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ ሰይመዋል፡፡
እንደ አቶ አለምአንተ ገለጻ በሆሳዕና ሥምምነት መሠረት ውይይት የተደረገባቸው ሃሳቦችና የተሰጡት አቅጣጫዎች በትብብር ጥምረቱ አማካኝነት ለሚመለከታቸው ሁሉም አካላት እንዲደርስ ይደረጋል፡፡
ፍትሕ ሚኒስቴር የትብብር ጥምረቱ ሰብሳቢ እና አገር አቀፍ የወንጀል መከላከልን እንደሚያስተባብር ተቋም ትላልቅ አገራዊ የቤት ስራዎችን ከንቅናቄ መድረኩ ተቀብሎ መመለሱን የተናገሩት አቶ አለምአንተ፤ በተለይም የኢትዮጵያውያን ፍልሰተኞች መተላለፊያና መዳረሻ ከሆኑ አገራት ጋር በሕግ ጉዳዮች ጠንካራ ትብብር የመፍጠር፤ የወንጀል ምርመራን የማጠናከር፤ በደቡብ ክልል ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ጠንካራ የትብብር ማዕቀፎችን መዘርጋት እንዲሁም በጥናት ላይ የተመሰረቱ ሥልጠናዎችን መስጠት የሚሉትን ለአብነት አንስተዋል፡፡
እንደ ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተሰጡትን የቤት ሥራዎች በአግባቡ ለመወጣት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ሁኔታ የሚንቀሳቀስ ይሆናል፡፡
በተያያዘ የመንግሥት ሕግና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ በተለያዩ የሕግ ጉዳዮች ዙሪያ በዚህ ዓመት ሊያካሂድ በዕቅድ የያዛቸው አምስቱ ትላልቅ አገራዊ መድረኮች የዝግጅት ሂደት ተገምግሟል፡፡
በዚሁ መሠረትም የመድረኮቹ አዘጋጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሔኖክ የዝግጅት ሥራዎቹን አቅርበው ውይይት የተካሄደበት ሲሆን፤ የእስካሁን አፈጻጸሙም የተሻለ መሆኑ ተመላክቷል፡፡ ቀጣይ አቅጣጫዎችም ተቀምጠዋል፡፡
በዚሁ መድረክ ላይ የብሔራዊ የትብብር ጥምረት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብርሃም አያሌው ከክቡር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አለምአንተ እውቅናና ሽልማት ተበርካቶላቸዋል፡፡
አቶ አብርሃም ከተሾሙ ጀምሮ ባለው አጭር ጊዜ ውስጥ የጽ/ቤቱን ሥራ ለማሻሻል እያደረጉ ላለው ጅምር ጥረት፤ ፍትሕ ሚኒስቴር በትብብር ጥምረቱ ውስጥ ያለውን የመሪነትና የማስተባበር ሚና በአግባቡ እንዲወጣ ከጥምረቱ አባል ተቋማት ጋር በአጭር ጊዜ እየፈጠሩ ያለው ትስስር፤ በጥምረቱ አሠራር ላይ ብዥታ የተፈጠረባቸውን ጉዳዮች የሚያጠራ የሕግ አስተያየትና ውሳኔ በፍትሕ ሚኒስቴር በኩል ለሚመለከታቸው እንዲተላለፍ በማድረጋቸው እንዲሁም ወንጀሉን በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ እንደትብብር ጥምረት ያሉ ቁልፍ ችግሮችን ለይቶ በሆሳዕናው መድረክ በማቅረብ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቅጣጫ እንዲያስቀምጡባቸው ላደረጉት አስተዋጽኦ ነው ሽልማቱ የተበረከተላቸው፡፡
ሽልማቱ አቶ አብርሃም ደረጉትን ጅምር ትረት ዕውቅና የሰጠና ለበለጠ ሥራ የሚያበረታታቸው ከመሆኑም በላይ ሌሎችንም የስራ ክፍል መሪዎች የሚያነቃቃ ነው ተብሏል፡፡