በመድረኩ ላይ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ የተከበሩ አቶ ታገሰ ጫፎ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር በፍትሕ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የማህበረሰቡ እርካታ ዝቅተኛ መሆኑን ገልፀው ህዝቡ በፍትሕ አገልግሎት ላይ ያለውን ቅሬታ በመሠረታዊነት ለመፍታት መንግሥት አቅጣጫ አስቀምጦ እየሰራ መሆኑን አመላክተዋል።
በዚህም መሠረት የፍትሕ አካላት የሶስት ዓመት ዕቅድ እንዲሁም የዳኝነት አካሉ የሶስት ዓመት ሮድ-ማፕ ተዘጋጅቶ ወደ ትግበራ መግባቱን አስታውሰው ትግበራውንም በበላይነት በፌደራል ደረጃ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚመራው፤ በክልሎች ደረጃም በክልል ምክር ቤት አፈጉባኤ እንደሚመራ በመግለጽ በመድረኩ የተገኙት የፌደራል እና የክልል የሕግ እና ፍትሕ ጉዳየች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች ይህን እቅድ በልዩ ሁኔታ ቁጥጥር፣ ክትትል እና ድጋፍ እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡
በመድረኩ ላይ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የሶስት ዓመት የትራንስፎርሜሽን (ሮድ-ማፕ) እና የፌዴራል አስተዳደር ስነ-ስርዓተ አዋጅ አተገባበርን ተከትሎ በፍትሕ ሚኒስቴር በኩል እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ቀርበው በጉዳዮቹ ላይ የፌደራልና ክልሎች ምክር ቤቶች ሚና ምን መሆን እንደሚገባ ውይይት ተደርጎባቸዋል።
በመጨረሻም በፌደራል የሕግ እና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ እፀገነት መንግስቱ እና በምክትል ሰብሳቢው የተከበሩ አቶ ኢሳ ቦሩ አማካኝነት የመዝጊያ ንግግር ተደርጎ የወደፊት አቅጣጫ ተቀምጧል።