የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐ/ሕግ ዘርፍ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ እንዲሁም የድሬደዋ እና የሀዋሳ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች በ2017 በጀት ዓመት 6 ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ላይ በትላንትናው ዕለት ውይይት ተደርጒል፡፡
የፍትሕ ሚኒስቴር የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥና የህብረተሰቡን ጥቅሞች ለማስከበር ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል አንደኛው በሆነው የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የወንጀል ምርመራ፣ክስና ክርክሮችን በማከናወን ፍህት እንዲሰፍን ከማድረግ አኳያ በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ 6 ወራት የተከናወኑ ተግባራት አፈፃፀም ሪፖርት የሚመለከታቸው የቅርንጫፍ ጽ/ቤት የስራ ሀላፊዎችና የቡድን መሪዎች በተገኙበት የእቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጓል፡፡
በንፋስ ስልክ ላፍቶ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የተካሄደውን መድረክ የመሩት በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር በጠቅላይ ዐ/ሕግ ዘርፍ የቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ጉዳይ ማስተባበሪያ ዳሬክቶሬት ዳሬክተር አቶ ጌቱ ታደሰ ባደረጉት ገለፃ በበጀት አመቱ የወንጀል ፍትሕ አገልግሎት አሰጣጥ አቅምንና ተደራሽነትን ለማሳደግ፤ ምርመራቸው ተጠናቀው ለቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ለውሳኔ ቀርበው መወሰን ያለባቸውን 27,019 የምርመራ መዝገቦች ውስጥ 97% በሚሆኑ መዛግብት ላይ ውሳኔ ለመስጠት ታቅዶ በ26,757 ወይም (99.03%) መዝገቦች ላይ በቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ውሳኔ መስጠት መቻሉና ይህም ከባለፈው ዓመት አንፃር 3,646(13.6%) መዛግብት ዐቃቤ ሕግ ጭማሪ ውሳኔ የሰጠባቸው መሆኑንና የውዝፍ ምጣኔውንም ከ6.6% ወደ 0.97% ማውረድ እደተቻለ ጠቅሰዋል፡፡
በሪፖርቱ በኢኮኖሚ ፣በሙስና ፣ በተደራጁ እና ድንበር ተሻጋሪ ፣በልዩ ልዩ ወንጀሎች እንዲሁም በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች የምርመራ መዛግብት ላይ ውሳኔ በመስጠት ከማጥራት አኳያ የማጥራት ምጣኔ አፈፃፀማቸው ከተያዘው እቅድ አንፃር መልካም አፈፃፀም የተመዘገበባቸው እንደሆነ ማወቅ ተችሏል፡፡ ከዚህም አንፃር በቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ያለውን የሠው ኃይል እጥረት ሸፍኖ በርካታ መዛገብት ላይ ዐቃቤ ሕግ ውሳኔ እንዲሰጥበት በማድረግ መልካም አፈፃፀም ማሰመዝገብ መቻሉ እንደ ጥንካሬ የሚጠቀስ መሆኑን እና የሚስተዋሉ የመረጃ አያያዝ ክፍተቶች ደግሞ በቀጣይ ትኩረት ተደርጎ ሊሰራባቸው እንደሚገባ በውይይት መድረኩ ተጠቁሟል፡፡
የሰብዓዊ መብትን የማክበር አፈፃፀምን በሚመለከት በ6 ወራት ውስጥ፤ በአጠቃላይ ለ9953 ተጠርጣሪዎችን በማረሚያ ቤት ተገኝቶ በመጎብኘት የታዩ ችግሮች ተለይተው መፍትሔ እንዲሰጣቸው ለማድረግ የተቻለ መሆኑ በውይይቱ ወቅት የተመላከተ ሲሆን፤ በተያያዘም በተለያዩ ቅርንጫፍ ጽ/ቤጾች አማካኝነት አዲስ አበባን ጨምሮ ድሬደዋ እና ሀዋሳ ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈፅመዋል በተባሉ የፖሊስ አባላት ላይ ምርመራ እንዲደረግባቸው ውሳኔ መሰጠቱ ተገልፆል፡፡
በመጨረሻም በቀረበው ሪፖርት ላይ ሰፋ ያለ ውይይት የደረገ ሲሆን፣ በፍትሕ ሚኒስቴር በጠቅላይ ዐ/ሕግ ዘርፍ የቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ጉዳይ ማስተባበሪያ ዳሬክቶሬት ዳሬክተር አቶ ጌቱ ታደሰ ባስተላለፉት መልዕክት ሁሉም አካላት የተጣለባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ በማሳስብ እንዲሁም ቀጣይ የስራ አቅጣጫዎችን በመስጠት የእቅድ አፈፃፀም ውይይቱ ተጠናቋል፡፡