የፍትሕ ሚኒስቴር በአፋር ክልል የማህበረሰብ የፍትህ አገልግሎት ማእከለን ለማጠናከር ያለመ ቅንጅታዊ የውይይት መድረክ እና ስልጠና አካሄደ

Ministry of Justice Conducts Consultative Forum and Training in Afar Region to Strengthen Community Based Justice Services

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር በአፋር ክልል ውስጥ ከተለያዩ የፍትሕ ተቋማት እና የዳኝነት አካል ጋር በመሆን ውይይት አካሂዷል፡፡ ውይይቱ በክልሉ ውስጥ ያሉ የኅብረተሰብ ፍትሕ ማዕከላትን (Community Justice Centers) እና የተቋማዊ ትብብርን ለማጠናከር የተካሄደ ነው፡፡

በውይይቱ ላይ የአፋር ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት፣ የፍትሕ ቢሮ ሃላፊ፣ የፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር እና የማረሚያ ቤት ኮሚሽን ተወካዮች የሳተፉ ሲሆን፣ የኅብረተሰብ ፍትሕ አገልግሎቶችን አቅም በማሻሻል የፍትሕ ተደራሽነት ለማረጋገጥ በትኩረት መሥራት ይገባል ተብሏል፡፡

በፍትሕ ሚኒስቴር የፍትሕ ሥርዓት ማሻሻያ እና የለውጥ አመራር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ኖህ ታከለ በመድረኩ ባስተላለፉት መልዕክት፤ በሀገር ደረጃ በፍትሕ ዘርፉ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት የ3 ዓመት የፍትሕ ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ትግበራ ሁለት ዓመት እንደሞላው ገልጸው፣ በፍኖተ ካርታው ከሚተገበሩ አምዶች ውስጥ አንዱና “የመሰረተ ማኅበረሰብ አቀፍ ፍትሕ አገልግሎትን ማሳደግ” ዋነኛው መሆኑን ጠቅሰዋል።

አያይዘውም ይህን አምድ ተግባራዊ ለማድረግ የፍትሕ ሚኒስቴር በርካታ ስራዎችን እየሰራ የሚገኝ ሲሆን፣ይህ መድረክም የእቅዱ አንዱ አካል በመሆኑ ሽማግሌዎች ስለሰብዓዊ መብቶችና ህገ-መንግስቱ ያላቸውን ግንዛቤ ማጎልበት የተሻለ ማኅበረሰብ ላይ የተመሰረተ የፍትሕ አሰጣጥን የሚያመቻችና ባህላዊ የግጭት መፍቻ ዘዴዎችን ከሀገር ሕግ መስፈርቶች ጋር የሚያስማማ መሆኑን ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል በማኅረሰብ ፍትሕ አገልግሎት መስጫ ማዕከል ውስጥ ለሚያገለግሉ የአፋር ክልል ሽማግሌዎች ሰብዓዊ መብትን በተመለከተ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናም በሰመራ ከተማ ተሰጥቷል።

የሥልጠናው ተሳታፊ የሆኑት የአፋር ሽማግሌዎች በበኩላቸው ፍትሕ ሚኒስቴር የሥልጠና መድረኩን በማመቻቸቱ አመስግነው፤ ሥልጠናው መሠረታዊ መብቶችን በማስከበር ማህበረሰቦቻቸውን በተሻለ መንገድ ለማገልገል እንደሚረዳቸውም አስታውቀዋል። አክለውም እነዚህን የአቅም ግንባታ ፕሮግራሞች ወደ ተጨማሪ የአፋር አከባቢዎች በማስፋት፣ በባህላዊ የፍትሕ ስርዓቶች እና በመንግሥታዊ የሕግ መስፈርቶች መካከል ያለውን ግንኙነት እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።

የውይይት መድረኩ ማኅበረሰብ አቀፍ የፍትሕ አገልግሎት አሰጣጥን ለማስፋፋት ቀጣይነት ያለው ትብብርና የጋራ ጥረት እንዲደረግ ስምምነት ላይ በመድረስ ተጠናቋል።

የቅንጅት እና የሥልጠና መድረኩ ሂል ኢንስቲዩት እና ዴስቲኒ ኢትዮጵያ ባደረጉት ድጋፍ መካሄዱ ተጠቁሟል።

የቅርብ ጊዜ ዜናዎች