የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ከፌዴራል ሕግና ፍትሕ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር በ2015 ዓ.ም ለተሾሙ ዐቃቤያነ ሕግ ሲሰጥ የነበረው የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠና ተጠናቀቀ።
ለአንድ ወር ያህል በተሰጠው በዚህ ሥልጠና በሽብር ፣ሙስና ፣ታክስና ጉምሩክ፣ በሰዎች መነገድና ሰዎችን በህገ ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀል ፣የኮምፒውተር ወንጀል ጉዳዮች ዙሪያ ሥልጠና መሰጠቱ ተገልጿል።
የሥልጠናውን መጠናቀቅ አስመልክቶ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የተቋም ግንባታና ሪፎርም ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኤርሚያስ የማነብርሐን ባስተላለፉት መልዕክት ዐቃቤያነ ሕግ በእውቀት፣ በክህሎት ፣በአመለካከት እና በስነምግባር የታነጹ መሆን አለባቸው ብለው ሥልጠናው ሰልጣኙን ውጤታማ በሚያደርግ መልኩ እንደተሰጠ ተረድቻለው ብለዋል። ዶክተር ኤርሚያስ አያይዘው በቀጣይ ወደስራ ክፍላችሁ ስትመለሱ በሥልጠናው ያገኛችሁትን እውቀት እና ክህሎት የበለጠ በማዳበር የተቋማችሁን ተልዕኮ እንደምታሳኩ እምነቴ ነው ብለዋል፡፡
በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የሕግና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አለም አንተ አግደው በመድረኩ እንዳሉት ሰልጣኞች አንድ ዓመት በስራ ላይ ቆይታችሁ በሥልጠናው የተለያዩ ጥያቄዎችን ለማንሳት እና በትምህርትና በስራ አለም ላይ ለገጠማችሁ ነገሮች ምላሽ ለማግኘት እድል ያገኛችሁበት ሥልጠና መሆኑን ተረድቻለው ብለው ፍትሕ ሚኒስቴር የአገሪቷ የሕግ አስፈጸሚ እና የመንግሥት ሕግ አማካሪ መሆኑን ገልጸው ይህንን ተቋማዊ ተልዕኮ እንደ ባለሙያ ለመወጣት መዘጋጀት ይጠበቅባችኋል ብለዋል፡፡
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕግና ፍትሕ ኢኒስቲቲዩት ምክትል ዳይሬክተር አቶ ዘካሪስ አርኮሎ ሥልጠና በራሱ ግብ አለመሆኑን ተቅሰው የወሰዳችሁትን ሥልጠና መነሻ በማድረግ ራሳችሁን ብቁ ባለሙያ ማድረግ ይጠበቅባችኃል ብለዋል፡፡
የሰልጣኞ ተወካይ አቶ ናትናኤል በሥልጠናው ዓይናችንን የሚገልፅልን ነገር አግኝተናል አንደዚህ አይነት ሥልጠናዎች ቀጣይነት ቢኖራቸው መልካም ነው ብሏል፡፡
በስተመጨረሻም ሥልጠናው ተከታትለው ላጠናቀቁ ዐቃቤያነ ሕግ የምስክር ወረቀት ተበርክቷል።