የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር ከፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ጋር በመሆን የይቅርታ መጠየቂያ በመንግሰት የኢ-ሰርቪስ ፖርታል ላይ አገልግሎት ግንቦት 22 ቀን 2ዐ15 ዓ.ም በቃሊቲ ማረሚያ ቤት አስጀምሯል፡፡
የፍትሕ ሚኒስቴር የተቋም ግንባታና ሪፎርም ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኤርሚስ የማነብርሃን እንደገለጹት የፕሮግራሙ ዋና ዓላማ የይቅርታ መጠየቂያ ስርዓትን ዘመናዊ በማድረግ በተለይም ይቅርታ የሚጠይቁ ታራሚዎች የይቅርታ ፎርም ለመሙላት በአካል ፍትሕ ሚኒስቴር መገኘት የነበረባቸውን ሂደት በማስቀረት ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል፡፡ ዶክተር ኤርሚያስ አያይዘውም ቤተሰብ የሌላቸው ታራሚዎች ጉዳያቸውን የሚከታተልላቸው ሰው በማጣት ምክንያት የይቅርታ መጠየቂያ ስርዓቱ ተጠቃሚ ለመሆን እንዳይቸገሩ የሚያደርግ ስርዓት በማበልጸግ ወደ ስራ እንዲገባ መደረጉን ተናግረዋል፡፡ የኢ-ሰርቪስ አገልግሎት ስራ መጀመሩ ብዙ ስራዎችን የሚያቀል መሆኑን ያወሱት ሚኒስትር ዴዔታው ስራው መጀመሩ የይቅርታ ስርዓት መስፈርቱን ለሚያሟሉ ታራሚዎች ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አገልግሎቱን ለመስጠት ቁርጠኛ መሆኑን የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አክለውም ፍትሕ ሚኒስቴር ለማረሚያ ቤት ኮሚሽኑ አስፈላጊ ግብአቶችን ድጋፍ እንደሚያደርግም ጠቁመዋል፡፡
በፍትሕ ሚኒስቴር የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና የመዝገብ አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፀጋዬ አማረ ባደረጉት ንግግር የመንግሥት ኤሌክትሮኒክስ ፖርታል ላይ የይቅርታ መጠቂያ ኢ-ሰርቪስ አገልግሎት መጀመሩ የሕግ ታራሚዎችንና የቤተሰባቸውን እንግልትና ድካም የሚያስቀር እንደሆነ ገልጸው ይህን ኢ-ሰርቪስ አገልገሎት በሁሉም በፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ሆነው አገልግሎቱን መስጠት የሚያስችሉ ባለሙያዎች በቂ ሥልጠና ወደስደው ወደ ሰራው መግባታቸውን አውስተዋል፡፡
የፌደራል ማረሚያቤት ኮሚሽን ኮሚሽነር ክቡር ዳመነ ዳሮታ በበኩላቸው እንደገለጹት የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ከሚነሳባቸው ጉዳዮች አንዱ የይቅርታ ሥርዓት ነው፤ ይህንንም ችግር ለመቅረፍ ዛሬ ከፍትሕ ሚኒስቴር ጋር ያስጀመርነው ስርዓት የተጠቀሰውን ችግር ለመቅረፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አውስተዋል፡፡ አክለውም የበለጸገው የይቅርታ ስርዓቱ ሳይቆራረጥ እንዲቀጥል ገልጸዋል፡፡
በመርሀ ግብሩ የይቅርታ ቦርድ ፅህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ሰናይት እንየው እና የፌደራል ማረሚያ ቤት አመራሮች ተገኝተዋል፡፡