በውጤታማ ተግባቦት እና የሕዝብ ግንኙነት ሳይንሳዊ መርሆች ላይ ያተኮር ሥልጠና ለፍትሕ ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት የሕዝብ ግንኙነት እና ኮሙኒኬሽን የስራ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች ተሰጥቷል፡፡
በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽ ዳሬክቶሬት የተዘጋጀው ይህ ሥልጠና በፍትሕ ሚኒስቴር እና በተጠሪ ተቋማት የሚገኙ የሕዝብ ግንኙነት እና ኮሙዩኒኬሽን የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም ባለሙያዎችን ሙያው በሚጠይቀው ልክ በአመለካከት፣ በእውቀትና ክህሎት የበቁ እንዲሆኑ በማድረግ የተቋሙን ስራዎች፣ ወቅታዊ ክስተቶችን እና ሁነቶችን በፍጥነት በመረዳትና በመገንዘብ በአግባቡ አደራጅተው ለህብረተሰቡ ተደራሽ እንዲያደርጉ በማስቻል ላይ ያለመ መሆኑን በፍትሕ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት እና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ትህትና ጎአ በሥልጠና መድረኩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ገልጸዋል፡፡
የሥልጠና መድረክ ላይ ተገኝተው በዘርፉ የቀጣይ ተግባራትን አቅጣጫዎች በማመላከት የመክፈቻ ንግግር ያደረኩት የፍትሕ ሚኒስቴር አማካሪ ሚንስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ሴክተሩ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እየተካወኑ የሚገኙ ተግራትን በማጉላትና በማስተዋወቅ፣ ለህብረተሰቡ መድረስ የሚገባውን ትክክለኛ መረጃ በማድረስ ተዓማኒነትን ያተረፈ የፍትሕ ስርዓት እንዲገነባ በማድረግ የተቋሙን ብሎም የሀገርን ገፅታ በመገንባት ረገድ ዘርፉ ወሳኝና አዎንታዊ ሚና መጫወት የሚችል በመሆኑ ባለሙያው ይሄን ኃላፊነት በመረዳት ውጤታማ የሆነ ተግባቦት ለመፍጠር በታቀደና በተቀናጀ መንገድ ስራውን ማከናወን የሚጠበቅበት መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡ አክለውም በፍትሕ ስርዓቱ ውስጥ ውጤታማ የሆነ የተግባቦት ስራን ለማከናወን በፍትሕ ሚኒስቴር እና በተጠሪ ተቋማት የሚገኙ የኮሙኒኬሽን ስራ ክፍሎች በጋራ የሚሰሩበትን አግባብ በመፍጠር ወጥነት ያለውና የተናበበ የሕዝብ ግንኙነት ስራን ማከናወን አስፈላጊ መሆኑን በአፅንኦት አሳስበዋል፡፡
የሕዝብ ግንኙነት መሰረቶች፣አጀንዳ ቀረጻ እና የቀውስ ጊዜ ኮሙኒኬሽን በሚል ርዕስ የተዘጋጀውን ሥልጠና የሰጡት የመንግሥት የኮሙኒኬሽን አገልግሎት የፌዴራል ተቋማት አስተባባሪ የሆኑት አቶ እንዳለው ሙሉአዓለም እንደገለጹት በተቋም ውስጥ እንዲሁም በውጪ ውጤታማ የሆነ የተግባቦት ተግባራትን ለማከናወን የሚያስችሉ ከወቅታዊ ሁኔታዎች ጋር የተቃኙ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ሳይንሳዊ መርሆችን በማቅረብ ሰፊ ገለፃ አድርገዋል፡፡ በዚህም የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ሙያ ምንነትንና ባህሪያትን፣ መሠረታዊ የሕዝብ ግንኙት መርሆዎችን፣ አበይት የሕዝብ ግንኙነት ተግባራትና ክህሎቶችን፣ የቀውስ ጊዜ ኮሙኒኬሽን ተግባራትን እና ተያያዥነት ያላቸውን ርዕሰ ጉዳዮች ከሳይንሳዊ እንዲሁም በመስኩ ውስጥ ከሚስተዋሉ ወቅታዊ ክስተቶች ጋር አስተሳስረው በማንሳት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ሰጥተዋል፡፡
ቀጥሎ በችሎት ውሎዎች ዘገባ አሠራር ዙሪ የተዘጋጀውን ሥልጠና የሰጡት በፍትሕ ሚኒስቴር የፍትሕ ሥርዓት ማሻሻያ እና የለውጥ አመራር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ኖህ ታከለ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች የችሎት ውሎዎችን ዘገባ ሲያዘጋጁ ታሳቢ ማድረግ ስለሚገባው ጉዳዮች፤ ተጎጂዎችን፣ ተከሳሽን እና የሕግ አስፈፃሚ አካላትን ተግባራት በማካተት ሚዛናዊ የሆነ ዘገባ አዘጋጅቶ ስለማቅረብ፣ እንዲሁም አንድ ግለሰብ ወንጀል በመፈፀሙ ምክንያት በሕግ መጠየቁንና ለጥፋቱም ተመጣጣኝ ቅጣት የተወሰነበት መሆኑን ህብረተሰቡ እንዲገነዘብ ለማድረግ የሚስችል ዘገባ ስለሚዘጋጅበት አግባብ እና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን በምሳሌ በማጣቀስ ሥልጠና ሰጥተዋል፡፡
ቀጥሎም በፍትሕ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽ ዳሬክቶሬት የ9 ወራት የስራ አፈፃፀም ያጋጠሙ ተግዳሮቶችና የተሰጡ መፍትሄዎች በዳሬክቶሬቱ ዳሬክተር ወ/ሮ ትህትና ጎአ የቀረበ ሲሆን፤ አያይዘውም የእርስ በርስ ትስስርን በመፍጠር ስራን በጋራ ማከናወን እንዲቻል ቀደም ሲል ተደራጅቶና ተቋርጦ የነበረውን ተጠሪ ተቋማትን ያካተተ የሕዝብ ግንኙነት ፎረም አጠናክሮ ለማስቀጠል የሚያስችል አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡
በመጨረሻም በሥልጠና የተዳሰሱ ጉዳዮችን አስመልክቶ በተሳታፊዎች የተለያዩ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ተነስተው ምላሽና ማብራሪያ በሚመለከታቸው ሀላፊዎችና አስተባባሪዎች ምላሽ ተሰጥቶባቸው የጋራ መግባባት እንዲፈጠር ተደርጎ ዝግጅቱ ተጠናቋል፡፡