የፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ኤርሚያስ የማነብረሃን (ዶ/ር) ትላንት ሐምሌ 04 ቀን 2017 ዓ.ም ተጀምሮ ዛሬም በቀጠለው የተቋሙ ቡድን መሪዎች ሥልጠና ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት በተቋሙ ውስጥ ያሉ ሁሉም ሰራተኞች በስትራቴጂክ እቅድ ዝግጅት እና አፈፃፀም ላይ በተገቢው መሳተፍ እንዳለባቸው ገልፀዋል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታው አያይዘውም በተቋሙ ውስጥ የሚገኙ የቡድን መሪዎች በሥልጠና እቅድ መሠረት ተቋሙ በእቅድ ዙሪያ ሊያመጣ ያሰበውን ውጤት ግብ እንዲያሳካ የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸውም ተናግረዋል።
የፍትሕ ሚኒስቴር ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች የተቋሙን ስትራቴጂክ እቅድ በመሥራት ላይ መሆናቸውን ያነሱት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው ሰልጣኞች በሥልጠናው ተግባራዊ ልምምድ በማድረግ߹ ግልፅ ያልሆነላቸውን ነጥብ አንስተው በመወያየት ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩ፤ ተቋሙ እያቀደ ያለውን የአስርና የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ እንዲሁም የ3 ዓመት የልማት እቅድ ላይ ጥልቅ ተሳትፎ በማድረግ ሊመዘን፣ሠራተኛው ሊፈፅመው እና አመራሩ ሊያስፈፅመው የሚችል ዕቅድ ማውጣት ላይ ጉልህ ድርሻ እንዳላቸው አውስተው ሰልጣኞች ሥልጠናውን በትኩረት እንዲከታተሉ በአፅኖኦት ገልፀዋል፡፡
የለውጥ አመራር ምንነት ߹በፍትሕ ዘርፍ የስርዓት አስተሳሰብ ߹ስትራቴጂካዊ አመራር ߹በለውጥ አስተዳደር እና በፕሮጀክት አስተዳደር መካከል ያለው ግንኙነት ߹በለውጥ አስተዳደር ውስጥ የአመራር አስፈላጊነት እና የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ የሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች በዛሬው ሥልጠና የተዳሰሱ ሲሆን በተጨማሪም ሰልጣኞች የተቋሙን ራዕይ÷ ተልዕኮ እና እሴቶችን መሠረት በማድረግ በቡድን በመሆን ተግባራዊ ስራዎችን አከናውነዋል፡፡