በሲዳማ ክልል የፍትሕ አገልግሎትን ለማሻሻል የተሰሩ ስራዎች ተጎበኙ

Works to Improve Justice Services Inspected in Sidama Region

በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የሕግና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ በክቡር አቶ በላይሁን ይርጋ የተመራ የትራንስፎርሜሽን እቅድ ግብረ ኃይል በሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ሀዋሳ ከተማ በመገኘት በክልሉ በባለፉት ሁለት አመታት የትራንስፎርሜሽን ትግበራ የተገኙ ውጤቶች በተለይም በክልሉ ፍትሕ አገልግሎት አሰጣጥ ረገድ እና ወንጀልን ለመከላከል ቴክኖሎጂን ከመተግበር አኳያ የተሰሩ ስራዎችን ጎብኝቷል።

ጉብኝቱ የተጀመረው በሀዋሳ ከተማ የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ጽ/ቤት በመገኘት ሲሆን DARIS (Document Authentication and Registration Information System) ተግባራዊ በማድረግ የተገኙ ውጤቶችን ማየት ተችሏል። በዚህ መሠረት አሠራር ሥርዓቱ ከፌዴራል የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ጋር በመቀናጀት ቴክኖሎጂን በመጠቀም በተቀላጠፈና የተገልጋዮችን ጊዜ በሚቆጥብ መልኩ አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑ ታይቷል። ይህ አገልግሎት ከመጀመሩ በፊት ከሰነዶች ማጭበርበር ጋር ተያይዞ ሲስተዋል የነበረውን ችግር መቅረፍ እንደተቻለ በገብኝቱ ወቅት ተገልፆል።

ግብረ ሃይሉ በመቀጣይ ጉብኝት ያደረገው በሀዋሳ ከተማ ፍርድ ቤት የተተገበረውን የመረጃ አያያዝ ሥርዓት ሲሆን፤ በፍርድ ቤቱ የመዛግብት ቀጠሮ ለማወቅ የሚያስችል እና የእለት የችሎት መዛግብት ቀጠሮ የሚታይበት ቴክኖሎጂ ታይቷል። በዚህም ተገልጋዮች ለሚፈልጉት አገልግሎት የሚያስፈልጋቸውን መረጃ በቀላሉ እንዲያገኙ ማስቻሉን እና የግልጸነት አሠራር መዘርጋቱን መገንዘብ ተችሏል።

ሌላው የጉብኝቱ አካል የነበረው ወንጀልን በመከላከል ረገድ ቁልፍ ሚና በመጨዋት ላይ የሚገኘውና በከተማው ከንቲባ ጽ/ቤት የተዘረጋው የCCTV ካሜራ የመቆጣጠሪያ ማዕከል ሲሆን፣ በከተማው እና በአካባቢው የሚደረጉት እንቅስቃሴዎችን ለመከታተል፣ ተሽከርካሪን በመጠቀም የሚፈፀሙ የተደራጁ ወንጀሎችን ለመለየት፣ የንግዱ ማኅበረሰብ በግብይት ሥርዓቱ ከደረሰኝ አሰጣጥ ጋር ተያይዞ ያሉትን ማጭበርበሮች ለመከታተል፣ የትራፊክ አደጋ አድርሰው የሚያመልጡ ተሽከርካሪዎችን በመለየት ለፍርድ ቤት ክርክር ሂደት የሚያግዙ ማስረጃዎችን ለማቅረብ ትልቅ አስተዋዕፆ ያደረገ መሆኑን ለመገንዘብ ተችሏል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ በከተማው የሚፈፀሙ ወንጀሎችን በስድስት በመቶ ለመቀነስ ታቅዶ በአስራ አምስት በመቶ መቀነስ መቻሉን እና ይህ ስኬት የተመዘገበው በCCTV ካሜራ ጉልህ አስተዋዕፆ መሆኑን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ገልፆል።

በመጨረሻም ቡድኑ በሀዋሳ ከተማ የሚገኘውን የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል የሴቶችና ሕፃናት የአንድ ማዕከል የተቀናጀ አገልግሎት በመገኘት ጉብኝት አድርጓል። በዚህ መሠረት በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈፀሙ ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች፣ በማዕከሉ ጥቃት ለደረሰባቸው ተጎጂዎችዎች የህክምና አገልግሎት፣ የስነ ልቦና ምክር አገልግሎት እና የፍትሕ አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግ በመሰራት ላይ ያሉ ስራዎች መመልከት የተችሏል፡፡

ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው በጉብኝታቸው ወቅት የታዩ ለውጦች አበረታቻ መሆናቸውን ገልፀው በዚሁ በተጀመረው አግባብ ለበለጠ ውጤት እንዲተጉ ገልጸዋል።

ጉብኝቱ የተጠናቀቀው የኢፌዲሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የሀዋሳ ቅርንጫፍ አገልግሎት አሰጣጥ ሂደትን በመጎብኘትና ከስራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ጋር በመወያየት ነው።

Tagged Under: authentication case case management system Child Protection Crime Prevention digital digital justice document Document Authentication federal ministry of justice forensic evidence Gender-Based Violence hawassa city integrated service delivery Justice Justice System Reform management police commission reform region sidama Sidama Region system Technology technology in justice transformation plan women's health
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች