የፋይናንስ አገልግሎቶች መድብል/ኮድ ለማርቀቅ በተጠናው ጥናት በተለዩ የፖሊሲ ጉዳዮች ላይ የመንግስት ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ውይይት ተደረገ

High-Level Government Officials Discuss Policy Issues Identified in Study for Drafting Financial Services Code

የንግድ ህጉን የማሻሻል ሂደት ከረዥም ጊዜ ቆይታ በኋላ እውን ሆኖ አዲሱ የንግድ ሕግ አዋጅ ቁጥር 1243/2013 ሆኖ ወጥቶ በስራ ላይ ይገኛል፡፡ እ.አ.አ በ 1960 የወጣው የንግድ ሕግ 60 ዓመት ከሚጠጋ የአገልግሎት ጊዜ በኋላ በአዲስ መድብል ሲቀየር በጎ የነበሩትን ጎኖች ይዞ፣ የማያስፈልጉት አስቀርቶና አዳዲስ ዓለም የደረሰባቸውን ለውጦች አካቶ ለረዥም አመታት ሊያገለግል በሚችል መልኩ እንዲወጣ ተደርጓል፡፡

የንግድ ህጉ በሚሻሻልበት ጊዜ የመድብሉ መጽሀፍ ሶስት እና አራት ማለትም የባንክ ስራና የሚተላለፉ የገንዘብ ሰነዶችን እና መድህንን የሚመለከተው የመጽሀፉ ክፍል በባህሪው በአንድ ወጥ የሆነ ጉዳይ ላይ የሚያተኩሩ በመሆናቸው ከንግድ ህጉ ወጥተው የፋይናንስ አገልግሎት መድብል/ኮድ/financial service code/ በሚል እንዲወጣ በወቅቱ የቀረበውን ምክረ ሀሳብ በመቀበል የፋይናንስ አገልግሎት መድብ የጥናትና አርቃቂ ቡድን ተቋቁሞ ስራዎች ተጀምረው ነበር፡፡ የጥናት እና አርቃቂ ቡድኑ ከፍትሕ ሚኒስቴር፣ ከብሔራዊ ባንክ፣ ከመድህን ሰጪ ድርጅቶች፣ ከባንክ እና ኢንሹራንስ ማህበራት፣ ከዩኒቨርስቲ መምህራን፣ በግል ከሚሰሩ በዘርፉ ሙያ ያላቸው ግለሰቦች ተወጣጥቶ ተቋቁሞ ለስራው አመቺነት የባንክ ስራ እና የኢንሹራንስ ቡድን በሚል በሁለት ቡድን ስራዎችን ሲሰራ ቆይቶ ነበር፡፡ የጥናትና አርቃቂ ቡድኑ በውጭ አገር አማካሪዎች እየታገዘ መድብሉን ለማዘጋጀት በዘርፉ ያሉ ህጎችን የመለየት እና የኢኮኖሚ እና የሕግ ክፍተቶች ጥናት ሲሰራ ቆይቶ በሁለቱም ቡድኖች በመድን ዘርፉ እና በባንኪንግ ዘርፉ ያሉና መድብሉን ለማዘጋጀት ወሳኝነት ያላቸውን የፖሊሲ ጉዳዮች የመለየት ስራ ተሰርቷል። በጥናት የተለዩትን የፖሊሲ ጉዳዮቹ የሚዘጋጀው መድብል አካል አድርጎ ለማካተት በቅድሚያ የመንግሥትን አቅጣጫ የሚፈልጉ በመሆናቸው ከሚመለከታቸው ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ማድረግ አስፈላጊ ነበር።

ይህን መነሻ በማድረግ ግንቦት 23 ቀን 2015 ዓ.ም የመንግሥት ከፍተኛ አመራሮች ማለትም የኢፌዲሪ የፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ጌዴዎን ጢሞቴዎስ፣ በኢፌዲሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የመንግሥት ሕግና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዢ ክቡር አቶ ማሞ ምህረቱ እና ሌሎች የሚመለከታቸው ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት ስራው ያለበት ደረጃ ተገምግሟል፤ በተለዩት የፖሊሲ ጉዳዮች ላይ ውይይት ተደርጓል።

በውይይት መድረኩ እንደተገለፀው የጥናትና አርቃቂ ቡድኖቹ በዘርፉ ያለውን የገበያ ክፍተት፣, ከዘርፉ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ህጎች መለየት/legal audit/inventory እና የውጭ ተሞክሮ ዳሰሳ ስራ

ከባለፈው አንድ ዓመት ጀምሮ ሲሰራ ቆይቶ በአሁኑ ጊዜ ጥናቱ ተጠናቆ መድብሉ /ኮዱን የማርቀቅ ስራ ተጀምሯል።

በመድረኩ ላይ የተጘኑት የኢፌዲሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ጌዴዎን ጢሞቴዎስ የጥናትና አርቃቂ ቡድን አባላት እና ሌሎች በሂደቱ ድጋፍ ላደረጉ አካላት እያደረጉት ላለው አስተዋጽኦ የላቀ ምስጋናቸውን አቅርበው የፋይናንስ አገልግሎት መድብልን የማውጣት ዓላማ አገራችን በመድን እና ባንኪንግ ዘርፉ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እና እንደአገር በዘርፉ እየተከናወነ ያለውን ዘርፈ ብዙ ለውጥ የሚመራና ምላሽ መስጠት የሚያስችል በቂና ጥራት ያለው ማዕቀፍ እንዲኖራት ለማድረግ ያለመ መሆኑን ገልፀው በቀጣይ መድብሉን የማዘጋጀት ስራው ውጤታማና ጥራቱን በጠበቀ መልኩ እንዲከናወን ለማድረግ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እና ሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅርበትና በትብብር እንደሚሰራ ገልፀዋል።

በአጠቃላይ በመድረኩ የተገኙት በቀረቡት የፖሊሲ ጉዳዮች ላይ አሁን አገራችን በፋይናንስ ዘርፉ እያደረገች ካለችው ዘርፈ ብዙ ለውጥ እና ቀጣይ የመንግሥት አቅጣጫዎች ጋር በማገናኘት ሀሳባቸውን በሰፊው አካፍለው እና በቀጣይነት በሚደረገው የፋይናንስ አገልግሎት መድብሉ ዝግጅት ላይ የስራ አቅጣጫ ተሰጥቶ መድረኩ ተጠናቋል።

Tagged Under: alemante agdew audit bank Banking banking regulation code commercial Commercial Code development draft legislation financial financial sector reform Financial Services financial services code gideon timotheos Government Officials Insurance insurance regulation legal Legal Audit legal framework National national bank of ethiopia Policy Policy Development Regulation Regulatory Framework sector Services
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች