ባንጁል፣ ጋምቢያ – በፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ በላይሁን ይርጋ የተመራ የኢትዮጵያ ልዑክ ቡድን በአፍሪካ የሰዎችና ህዝቦች መብቶች ቻርተር (ባንጁል ቻርተር) ከ7ኛ እስከ 10ኛ የተጠቃለለ ወቅታዊ የኢትዮጵያ አፈጻፀም እና በአፍሪካ የሴቶች መብቶች ፕሮቶኮል (ማፑቶ ፕሮቶኮል) መነሻ ወቅታዊ አፈጻፀም ላይ ሪፖርቶችን ማቅረቡ ይታወሳል፡፡
በትላንትናው እለት ማለትም ግንቦት 4 ቀን 2017 ዓ.ም በነበረው መርሀ ግብርም ልዑክ ቡድኑ ከኮሚሽኑ ከቀረቡ 270 ጥያቄዎች ለአብዛኛዎቹ ምላሽ አቅርቧል።
ሪፖርቱ ኢትዮጰያን የአፍሪካ የሰዎችና የሕዝቦች መብቶች ቻርተር ወቅታዊ ሪፖርት ከሚያደርጉ ውስን ሀገራት ተርታ እንድትሰለፍ ያደረጋት መሆኑ ተመላክቷል፡፡
በመድረኩ ኢትዮጵያ በአገሪቱ የሰብዓዊ መብቶችን እና የጾታ እኩልነትን ለማጎልበት እና የሪፖርት ግዴታዋን ለመፈፀም ቁርጠኝነት ያሳየችበት መድረክ ነው፡፡
መድረኩም በትላንትናው እለት ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡