በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የፌደራል ህጎች ተፈፃሚነት መከታተያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሪት ሀወኒ ታደሰ የዳይሬክቶሬቱን የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያዉ ሩብ ዓመት አፈፃፀምን አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በማብራሪያቸዉም የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የአስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 1263/2014 አንቀጽ 40(5) እና በፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 943/2008 አንቀጽ 21(2) በተሰጠው ሥልጣን መሠረት የፌደራል ሕጎች ተፈጻሚነት እና የአስፈጻሚ አካላት ክትትል የሚወስን መመሪያ በፌደራል አስተዳደር ሥነ-ሥርአት አዋጅ ቁጥር 1183/2012 የተቀመጡትን ቅድመ ስነ-ስርዐት መሠረት በማድረግ ተዘጋጅቶ ተጠናቋል ብለዋል፡፡
ዳይሬክተሯ አያይዘዉም በመጀመሪያዉ ሩብ ዓመት በፌዴራል አስተዳደር ሥነ-ሥርአት አዋጅ ቁጥር 1183/2012 ተገዥነትን ለማሳደግ ለ67 የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ቱሪዝም ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች፣ ለ26 የኢ.ፌ.ዲ.ሪ መስኖና ቆላማ አከባቢ ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች፣ እና ለ 78 የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ውሃና ኤነርጂ ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች፣ በድምሩ 171 ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች በፌዴራል አስተዳደር ሥነ-ሥርአት አዋጁ ይዘት፣ ዓላማ እና ፋይዳ ላይ ሥልጠና በመስጠት ግንዛቤ ማሳደግ መቻሉንም ገልፀዋል፡፡
ለሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የአስተዳዳር ስነ-ስርዐት ሕግ ለማጸደቅ በተደረገ ድጋፍ እና ክትትል በክልሉ ህጉን ማፀደቅ መቻሉን አንስተዉ በእስካሁኑ ሂደት ህጉን ላላፀደቁ ክልሎች ተመሳሳይ ድጋፍ እየተሰጠ ይገኛል ሲሉም ለአብነት የቤንሻንጉል ጉምዝ እና የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትን አንስተዋል፡፡
ክትትልና ጥቆማን መነሻ በማድረግ የዲጂታል መታወቂያ በአዲስ አበባ ከተማ አሸከርካሪ እና ተሽከርካሪ ባለሥልጣን ላይ ያለውን አፈጻፀም አስመልክቶ የክትትል ስራ በመካሄድ ላይ እንደሚገኝም አስታውሰው ዳይሬክተሯ አክለዉም በመንግሥት ተቋማት ተደጋጋሚ የፋይናንሺያል ኦዲት ግኝት የሚሆኑ የሕግ ጥሰቶችን በመለየት የጥሰቶቹን ምክንያት መለየት እና የመፍትሄ ሀሳብ ለማቅረብ የሚያስችል ጥናት ወደ መጠናቀቁ መቃረቡን ገልፀዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የፌደራል ህጎች ተፈፃሚነትን ለማረጋገጥ የማኅበራዊ ጤና መድህን አዋጅ ቁጥር 690/2002፣ ደንብ ቁጥር 191/2002፣ ደንብ ቁጥር 271/2005ን፣ የማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አዋጅ ቁጥር 1273/2014 እና ደንብ ቁጥር 535/2015 አተገባባር ክትትል ለማድረግ የሚያስችል ስራ እየተሰራ ሲሆን በዋናነት በሀገር ዐቃፍ ደረጃ መረጃ የመሰብሰብ የማጠናቀቅ ስራ መሰራቱን የገለፁት ዳይሬክተሯ በ2017 ዓ.ም የመጀመሪያዉ ሩብ ዓመት እነዚህና ሌሎች መሰል ተግባራት በዳይሬክቶሬቱ ማከናወን መቻሉን ገልፀዋል፡፡