በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ለመከላከል የተዘጋጀው ስትራቴጂ ረቂቅ ሰነድ ከተለያዩ ተቋማት ለተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ቀርቦ ውይይት ተደረገበት፡፡
የሰነዱን መቅረብ አስመልክቶ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የመንግሥት ህገና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚንስቴር ዴኤታ አቶ አለምአንተ አግደው እንደገለጹት በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለመከላከል እና ወንጀል ፈጻሚዎችን ለሕግ ለማቅረብ ሀገር አቀፍ ስትራቴጂ ሰነድ መዘጋጀቱ ተገቢ መሆኑን ገልጸው ሰነዱ ላይ በጥልቀት ውይይት አድርጎ ግብአት ሊሆኑ የሚችሉ አስተያየቶችን መሰብሰብ እና ሰነዱ በተሻለ የተቀናጀ አገልግሎትን ለመስጠት በሚያስችል ደረጃ ተዘጋጅቶ እና ጸድቆ በፍጥነት ወደ ተግባር መግባት አለበት ብለዋል፡፡
ስትራቴጂ ሰነዱን ያቀረቡት ዶ/ር ዳንኤል ኃይሉ በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ከእለት ወደ እለት እየጨመረና እየተወሳሰበ የመጣ ወንጀል እንደመሆኑ ስትራቴጂው በሚዘጋጅበት ጊዜ ዓለም ዓቀፍ፣ ሀገር አቀፍ እና በአገራችን ያሉ አካባቢዎች ተሞክሮዎች ምን እንደሚመስሉ ቅኝት በማድረግ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ፣ ተግዳሮቶች እና መልካም ተሞክሮዎች በመቀመር፤ ስትራቴጂው ምን ማካተት እንዳለበት የሚያመላክት ዋና ዋና ሀሳብ የያዘ ሰነድ በቅድሚያ ተዘጋጅቶ ስምምነት ላይ መደረሱን ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም ስትራቴጂው ሲዘጋጅ የተለያዩ ሚንስቴር መ/ቤቶችን፣ የሲቪል ማህበራት እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የልማት አጋሮች እና ሌሎች ባድርሻ አካላትን እንዲሳተፉ ተደርጎ መዘጋጀቱንም አብራርተው ስትራቴጂው መንግሥት መር፣ በኢትዮጲያ የተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች መገለጫ ላይ መሠረት ያደረገ፣ ቀጣይነት ያለው፣ ወጪ ቆጣቢ እና መማር ላይ የተመሰረተ መርህ እንዲኖረው ተደርጎ መዘጋጀቱንም ጭምር ዶ/ር ዳንኤል አውስተዋል፡፡
ስትራቴጂው የተዘጋጀበት ዋና ዓላማም ከጾታዊ ጥቃት ተጋላጭነት ጋር የሚገናኙ ህጋዊ፣ የስነ ልቦናዊ፣ ማበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ፤ በፍህ ስርዓት ውስጥ ተዋናይ የሆኑትን የሕግ፣ ከማስቀጣት እና በዳኝነት ስራው ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎችን አቅም በማጎልበት ተጎጂ ሴትና ህጻናትን የፍትሕ አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ፤ በጾታዊ ጥቃት ጉዳት የደረሰባቸውን ሴቶችና ህጻናትን የማኅበራዊ አገልግሎት ድጋፍ ውጤታማ ለማድረግ እንዲሁም በተቋማት መካከል ቅንጅታዋ አሠራርን በማጠናከር የጋራ ዕቅድን ትግበራ ተቋማዊ ምዘና በጾታዊ ጥቃት ወንጀልን ከመከላከልና ጥቃት ከደረሰ በኋላ ቀልጣፋ ምላሽ ለመስጠት እንደሆነ ያብራሩ ሲሆን ሌሎች በስትራቴጂው ውስጥ የተካተቱ ዝርዝር ተግባራትን ለቤቱ አቅርበው ውይይት ተደርጎበበት ጠቃሚ ግብዓቶች ተሰባስበዋል፡፡በመጨረሻም የመንግሥት ሕግና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚንስቴር ዴኤታ አቶ አለምአንተ አግደው በስትራቴጂ ሰነድ ዝግጅቱ ላይ ተሳትፎ ላደረጉ ባለሙያዎች ሁሉ ምስጋናቸውን ካቀረቡ በኋላ ባስቀመጡት የስራ አቅጣጫ በተዘጋጀው ስትራቴጂ ሰነድ ውስጥ የመንግሥትን ትኩረት የሚፈልጉ ጉዳዮች እንዲለዩ፣ ሰነዱ የተዘጋጀው በእንግሊዘኛ በመሆኑ በአማርኛ ተተርጉሞ እንዲዘጋጅ በተጨማሪም ሰነዱን ያዘጋጁ አካላቶች በፍትሕ ሚንስቴር የሕግ ጥናት፣ ማርቀቅና ማጠቃለል ዳይሬክቶሬት ጋር በጋራ በመሆን የፖሊሲ ውሳኔ የሚፈልጉ ጉዳዮችን ለይተው እንዲያወጡ አቅጣጫ ሰጥተው የለቱ መርሃ-ግብር ተጠናቋል፡፡