የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ከጀርመኑ ጂ.አይ.ዜድ ጋር በመተባበር ያዘጋጀውና የአስተዳደር ስነ-ሥርዓት ሕግ ለሕግ የበላይነትና ለመልካም አስተዳደር ግንባታ ያለው ፋይዳና ተያያዥ ጉዳዮች የተዳሰሱበት በአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ሰመራ ከተማ ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የምክክር መድረክ ተጠናቋል።
የምክክር መድረኩ በዛሬው ውሎው በአስተዳደር ስነ ሥርዓት ሕግ አተገባበር ሂደት የፍርድ ቤቶች ሚና ንፅፅራዊ ቅኝት፣የፌደራል እና የክልሎች አስተዳደር ስነ ሥርዓት አዋጅ ይዘት ንፅፅራዊ ምልከታ የሚሉ ትንታኔዎች በዘርፉ ምሁራን እንዲሁም በስራ ሀላፊዎች አማካኝነት ቀርበው ሰፋ ያለ ውይይት ተካሂዶባቸዋል።
የምክክሩ ተሳታፊዎችም ምክክሩ ዝርዝር ተሞክሮዎችን የቃኘ ከመሆኑ በተጨማሪ በተለይም የአስተዳደር ስነ ሥርዓት አዋጁን ወደ ክልሎች አውርዶ ለመተግበር መሰል የምክክር መድረኮች የሚኖራቸው ሚና የላቀና ጠቀሜታቸው የጎላ መሆኑን አንስተው ከመጡበት ክልል ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት የአስተዳደር ስነ ሥርዓት ህጉ በክልላቸው የደረሰበትን ደረጃ አብራርተዋል፤ጥያቄዎቻቸውንም አንስተው በመድረኩ አዎያዮች አማካኝነት ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል።
በማጠቃለያው በሁለት ቀናት በርካታ ጉዳዮች ተነስተው ምክክር የተደረገባቸው ሲሆን ከዚህ በዘለለ የፌደራልና የክልል የፍትሕ አካላት ዕርስ በርስ በመገናኘት ልምድ በመለዋወጥ ረገድ የሚፈጥረው እድል የጎላ መሆኑን የገለፁት የፍትሕ ሚኒስቴር የመንግሥት ሕግና ፍትሕ አገልግሎት ሚኒስትር ዲኤታ ክቡር አቶ በላይሁን ይርጋ ለአንድ አገራዊ ለሆነ የፍትሕ ሥርዓት መሳካት በጋራ መሥራት ያስፈልጋል ሲሉ በመጨረሻም ምክክሩ በተሳካ ሁኔታ እንዲዘጋጅ ድጋፍ ላደረጉት ለጂ.አይ.ዜድ፣ ለፍትሕ ሚኒስቴር እና ለአፋር ክልል ፍትሕ ቢሮ አዘጋጆች ምስጋና አቅርበዋል።
በተያያዘ መርሃ ግብር የምክክር መድረኩ ተሳታፊዎች በአፋር ክልል በዱብቲ ከተማ በመገኘት ችግኝ ተክለዋል።