የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴርና የክልል ፍትሕ ቢሮዎች በጋራ መሥራት እንዳለባቸው ዛሬ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር አዘጋጅነተ በተካሄደው የጠቅላይ ዐቃቢያነ ሕግ የጋራ መድረክ ላይ ተገልጿል፡፡
በመድረኩ የፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞትዎስን ጨምሮ ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የክልል ፍትሕ ቢሮ ኃላፊዎች፣ የፍትሕ ሚኒስቴር ተጠሪ ተቋማት አመራሮች፣ የተለያዩ የፌደራል ተቋማት እንዲሁም የተቋሙ የስራ ኃላፊዎች የተገኙ ሲሆን በክብር እንግዳነት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ፣የፍትሕና ዴሞክራሲ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ እፀገነት መንግስቱ ተሳትፈዋል፡፡
የፍትሕ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞትዎስ በመድረኩ ንግግር ያደረጉ ሲሆን ከዚህ ቀደም መሰል የጠቅላይ ዐቃቢያነ ሕግ ጉባዔ ሲካሄድ እንደነበረ አስታዉሰው በተለያዩ ምከንያቶች የመድረኩን ተከታታይነት ማስጠበቅ ባለመቻሉ በሚፈለገው ልክ መንቀሳቀስ አልተቻለም ብለዋል፡፡
ዶ/ር ጌዲዮን ይህንን ሁኔታ ለመለውጥ ወጥና ቀጣይነት ባለው መንገድ በመገናኘት በተናበበ መልኩ ሕዝብን ማገልገል የሚያስችል ጠንካራ አሠራር ዘርግቶ በጋር መንቀሳቀስ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
በመድረኩ እንደተገለጸው ከዚህ ቀደም ከኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሕዝብ ተወካዮችና ከሚኒስትሮች ምክር ቤት፣ ከፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ ከምሁራን፣ ከሕግ ባለሙያዎች፣ ከሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶችና ከተለያዩ የማኅበረሰብ አካላት እንዲሁም ከባለድርሻ አካላት ጋር በተደረጉ ውይይቶች በሕግና በፍትሕ ጉዳዮች ዙሪያ ሀገር አቀፍ የሆነ የተቀናጀና የተናበበ ሥራ መሥራት እንደሚያስፈልግ በስፋት ይነሳ እንደነበረ ተገልጿል፡፡ ነገር ግን ችግሩን ለመቅረፍ በተቋም ደረጃ የክልል ጉዳዮችን በትኩረት የሚከታተል ዳይሬክቶሬት ከአንድ ዓመት በፊት በማቋቋም ወደ ስራ የተገባ ቢሆንም የሚፈለገዉን ዉጤት ማምጣት እንዳልተቻለ የተገለጸ ሲሆን ይህንን ሁኔታ በመለውጥ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተናበበና የተቀናጀ አሠራር በመዘርጋት የፌዴራል ስርዓቱን በጠበቀ መልኩ ወጥነት ያለው የፍትሕና የሕግ ሥርዓት መዘርጋት አስፈልጓል ተብሏል፡፡
ዜጎች በየትኛዉም የሀገሪቱ ክፍል ቢገኙ የሕግና ፍትሕ ስርዓቱ መብትና ጥቅማቸዉን የሚያስጠብቅ እንዲሁም ተደራሽና ቀልጣፋ ምላሽ የሚሰጥ ሊሆን እንደሚገባም ተገልጿል፡፡
ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከፖለቲካ ለውጡ ጋር ተያይዞ በሕግና ፍትሕ ዘርፉ የታዩ በጎ ለውጦችና ጅምሮች ቢኖርም በዚያው ልክ ክፍተቶች እንዳሉ የማይካድ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ጠንካራ፣ ውጤታማና ዘላቂ የሆነ ቅንጅታዊ አሠራርን መዘርጋት እንዲሁም ቅንጅታዊ አስራሩ ቋሚና ተከታታይ የሆነ የግንኙነት መድረኮች ያሉት፣ በበላይ አመራሮች ቢቻ ሳይሆን በየደረጃው ባሉ የሥራ ኃላፊዎች መኻከል ሊኖርና የዜጎችን የፍትሕ ጥማት ማዕከል ያደረገ ሊሆን ይገባል ተብሏል፡፡
ለዚህም እንዲረዳ የወንጀል ፍትሕ ሥርዓቱን ማዘመን፣ የተናበበና የተቀናጀ ሀገር አቀፍ የፍትሕ ዘርፍ እንዲኖር ማድረግ፣ ተቋማዊ ማሻሻያ ማድርግ፣ የማኅበረሰብ አቀፍ የፍትሕ አገልግሎት ማስፈን እንዲሁም የሽግግርና የተሃድሶ ፍትሕ አማራጮችን መተግበር እንደሚገባ ተገልጿል፡፡በተጨማሪም በመድረኩ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴርና የክልል ፍትሕ ቢሮዎች የጋራ ምክር ቤት የተቋቋመ ሲሆን የአሠራር ስርዓት ሰነድ ቀርቦ ውይይት የተደረገበት ከመሆኑም በላይ የጋር መግባቢያ ሰነድ ተዘጋጅቶ የፊሪማ ስነ-ስርዓትም ተካሂዷል፡፡