በትላንትናዉ እለት የጀመረዉና የሕግና የፍትሕ ማሻሻያዎችን አስመልክቶ ከክልሎች ጋር ልምድ ለመለዋወጥ እየተካሄደ ያለዉ ዉይይት እንደቀጠለ ነዉ፡፡
የተካሄዱ የሕግ ሪፎርም ስራዎች ወደ ክልሎች የሚወርዱበትን መንገድ አስመልክቶ እየተካሄደ ያለዉ ዉይይት በርካታ ርእሰ ጉዳዮች እየተነሱበትና ዉይይት እየተካሄደበት የቀጠለ ሲሆን ሀገር አቀፍ የሕግ እና የፍትሕ ማሻሻያ ከክልሎች አንፃር የሚዳስስ የዉይይት መነሻ ጽሑፍ የፌዴራል የፍትሕና የሕግ ኢንስቲቲዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ምትኩ ማዳ አማካኝነት ቀርቦ ውይይት ተደርጓል፡፡
ውይይቱን የመሩት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትሕና ዶሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ እፀገነት መንግስቴ እና በፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ አቶ አለምአንተ አግደዉ ናቸው፡፡
የፍትሕና የሕግ ማሻሻያዎች በሚሰሩበት ጊዜ ከክልሎች አንፃር ምን መምሰል አለበት የሚለዉን የመወያያ ጽሑፍ አቶ ምትኩ ሲያቀርቡ በፌዴራል ደረጃ የተደረጉ የሕግና ፍትሕ ማሻሻያ ስራዎች አጀማመር፣ ያለፈባቸዉን መንገዶች እና የስራዉን አጠቃላይ ሂደት ያቀረቡ ሲሆን በፌዴራል የወጡ አብዛኛዎቹ ህጎች የአፈፃፀም ወሰናቸዉ የአገሪቱን ግዛት የሚያካልሉ ስለሚሆኑ ከክልሎች ጋር በጋራ ከተሰራባቸዉ ተፈፃሚነታቸዉና ዉጤታማ የመሆን እድላቸዉ ሰፊ እንደሚሆንም አንስተዋል፡፡
ህጎቹ ሲረቀቁ ከመጀመሪያዉ ጀምሮ የነበረዉ የክልሎች ተሳትፎ ዉስን እንደነበር ያነሱት አቶ ምትኩ በጋራ ቢሰሩ ኑሮ የተሻለ ሁኔታን ይፈጥር እደነበር ገልፀዉ ከመጀመሪያዉ አብሮ ቢሰራ የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ፣ በመረዳዳት የሚኖረዉን ክፍተት ለማጥበብና ሙቀቱንና ግለቱን ጠብቆ ለመሄድ የራሱ የሆነ አስተዋፅኦ ይኖረዉ እንደነበር አስታዉሰዋል፡፡
ክልሎች ህብረሰተቡ ሁልጊዜ በለዉጥ ዉስጥ እንዳለ ታሳቢ በማድረግና የሕግ ማሻሻያ አስፈላጊ መሆኑን በመገንዘብ በፌዴራል ደረጃ የተወሰደዉን ማሻሻያ ልምድ ተሞክሮ በመዉሰድ ከዚህ በመነሳት ክልሎች ማሻሻያዎቹን ሲያደርጉ ከራሳቸዉ ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳትና የራሳቸዉን አደረጃጀት በማዋቀር አቅማቸዉን እየገነቡ ሊሰሩ እንደሚገባ ተመላክቷል፡፡
ቀጥሎም አዎያዮቹ ቅንጅታዊ አሠራርን በሚመለከት በቀጣይ በምን መንገድ እንስራ በሚሉና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የመፍትሄ ምክረ ሀሳቦችን እንዲሰጡ ለተሳታፊዎቹ መድረኩ ክፍት ያደረጉ ሲሆን በርካታ አስተያየቶችና ምክረ ሀሳቦች እንዲሁም ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡
የክልል ተሳፊዎችም የሕግ ማሻሻያ ስራዎቹ በዚህ መልኩ ለዉይይት መቅረባቸዉና በጋራ መሰባሰብና መወያየቱ በራሱ መልካም ጅምር መሆኑን ገልፀዉ በተለይም ህጎቹ ወደ ክልል ወርደዉ ማሻሻያ እንዲደረግባቸዉ መታቀዱ በተለይም ሕዝብን በማሳተፍ ረገድ እና ለተግባራዊነቱ የራሱ የሆነ አዎንታዊ ጎን እንደሚኖረዉ በመግለፅ በፍትሕ ሚኒስቴር በኩልም ተገቢዉን አገዛ የመስጠቱ ጉዳይ ሊታሰብበት እንደሚገባ በመጠየቅ የወጡ ህጎችን ግንዛቤ በመፍጠር ረገድ የግንዛቤ የማዳበሩ ስራም ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
የተነሱ ጥያቄዎችንና ሀሳብ አስተያየቶችን አስመልክቶ ምላሽና ማጠቃለያ የሰጡት የፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ አቶ አለም አንተ አግደዉ ክልሎች በሚያሻሽሏቸዉ ህጎች በተለይም ሕዝብን አሳታፊ እያደረጉ መሄድ ዋነኛዉ ተግባር ሊሆን እንደሚገባ በመጠቆም የሚወጡ ህጎች ፍትሀዊነት እና የሕዝብ ቅቡልነት ያላቸዉ እንዲሆኑ ማድረግም አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡አያይዘዉም ወንጀለኞች ድንበር ተሻግረዉ ከአንድ አገር ወደ ሌላ አገር በትብብር እየሰሩ ባሉበት በዚህ ዘመን ከፌዴራል እስከ ክልል ያለዉ የፍትሕ መዋቅርም በደንብ በመተባበርና በመደጋገፍ መንፈስ ሊሰሩ እንደሚገባ ያሳሰቡ ሲሆን ለዚህም ኃላፊነትን በአግባቡ መወጣት፣ የአመራር ቁርጠኝነትና በመተማመን የህዝቡን ድጋፍ ይዞ መሥራት ዉጤታማ እንደሚያደርግ ለተሳታፊዎቹ አብራርተዋል፡፡