የኢትዮጵያ መንግሥት የሽግግር ፍትሕን ተግባራዊ ማድረግ ለአገራችን ዘላቂ ሰላም፣ ዲሞክራሲ እና ፍትሕ የሰፈነበት ሥርዓት ግንባታ ጉልህ ሚና የሚጫወት መሆኑን በመገንዘብ ሂደቱን በተሟላና በተቀናጀ መልኩ ለመተግበር የሚያስችሉ የተለያዩ ስራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል። በዚህ ረገድ የሽግግር ፍትሕ የሚመራበት ፖሊሲ የማዘጋጀት ስራ ለመጀመር የሚያስችለው የሽግግር ፍትሕ የፖሊሲ አቅጣጫ አማራጮች መነሻ ሰነድ በፍትሕ ሚኒስቴር በተደራጀው ከፍተኛ የባለሙያዎች ቡድን ተዘጋጅቶ በተለያዩ የምክክር መድረኮች ግብዓት የማሰባሰብ ስራ በመሰራት ላይ ይገኛል።
የሽግግር ፍትሕ የፖሊሲ አቅጣጫ አማራጮች ሰነድ ግንቦት 29 ቀን 2015 ዓ.ም ከትግራይ ክልል ፍትሕ ቢሮ እና ፍርድ ቤት ለተውጣጡ የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል። ሰነዱን ያቀረቡት የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ አዘጋጅ ገለልተኛ የባለሙያዎች ቡድን አባላት ሲሆኑ በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች በፖሊሲ አቅጣጫ አማራጮች ላይ ያላቸውን ጥያቄና አስተያዬት አንስተው ውይይት የተደረገ ሲሆን በውይይት መድረኩ ሰነዱን ለማዳበር የሚረዱ የተለያዩ ጠቃሚ አስተያየቶች ቀርበው ግብዓቶችን የማሰባሰብ ስራ ተሰርቷል።
በመጨረሻም የመንግሥት የሕግ እና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አለምአንተ አግደው የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ዝግጅቱ ገና በጅምር ላይ ያለ በመሆኑ በቀጣይ በስፋት በክልሉ የምክክር መድረኮች የሚደረጉ መሆኑን አስረድተው ከፍትሕ ቢሮው እና ከፍርድ ቤቶች ጋር በቅርበት ስለሚሰሩባቸው የትብብር ማዕቀፎች ገለጻ አድርገው ውይይቱ ተጠናቋል፡፡