በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ተስፋዬ ዳባን ያካተተ የአገራዊ የፍትሕ ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን የድጋፍና ክትትል ቡድን የቤንሻንጉል ጉምዝ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የፍትሕ ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አፈፃፀም ያለበትን ደረጃ ገምግሟል፡፡
በመድረኩ የፍትሕ ተቋማት ቀልጣፋ እና ፍትሐዊ አገልግሎት መስጠት አንዲችሉ ከ2016 ጀምሮ የፍትሕ ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ትግበራ ከተጀመረ ወዲህ እንደ አገር የፍትሕ ሥርዓቱ አገልግሎት አሰጣጥ እየተሻሻለ መምጣቱን እና የዜጎች የፍትሕ ጥያቄ በመመለስ ረገድ አበረታች ስራዎች መከናወናቸው ተገልጿል፡፡
ባለፉት ሁለት ዓመታት በክልሉ በተተገበረው የፍትሕ ትራንሰፎርሜሽን ዕቅድ አበረታች ውጤት የተመዘገበ መሆኑ በተለይም የክልሉን ነባር ብሔረሰቦች ባህላዊ የዳኝነት ሥርዓት ማቋቋሚያ አዋጅ ለክልሉ ምክር ቤት አቅርቦ ማፀደቅ ከመቻሉ በተጨማሪ በተመረጡ ወረዳዎች ላይ ባህላዊ የዳኝነት አካላት የማደራጀት ሥራ መሠራቱ፣ የክልሉን አስተዳደር ሥነ -ሥርዓት አዋጅ በማርቀቅ ማጽደቅ መቻሉ ተገልጿል::
በተያያዘም የፍትሕ ተቋማት በትራንስፎርሜሽን ቀሪ አንድ ዓመት ዕቅድ የተያዙ ተግባራትን ለማሳካት የታዩ ውስንነቶችን በመቅረፍ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ተግባራት በመለየት ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባ የተገለጸ ሲሆን በክልሉ በሴቶችና ሕጻናት ላይ የሚፈጸም ወንጀልን ለመመርመርና ለተጎጂዎች የተቀናጀ የሥነ ልቦና፣ የሕክምና እና የሕግ አገልግሎት ለመስጠት የተደራጀው የተቀናጀ የአንድ ማዕከል አገልግሎት እና በክልሉ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ሥራዎች በልዑክ ቡድኑ ተገብኝተዋል፡፡