6ኛው የፍትህ ሚኒስቴር እና የክልል ፍትህ ቢሮዎች የጋራ ጉባኤ በሀዋሳ ከተማ በመካሔድ ላይ ይገኛል

6th Joint Conference of the Ministry of Justice and Regional Justice Bureaus Being Held in Hawassa City

“ማኅበረሰብ አቀፍ የፍትሕ አገልግሎት ለተሻለ የተገልጋይ እርካታ“ በሚል መሪ ሀሳብ ለ6ኛ ዙር እየተካሄደ ያለው የፍትሕ ሚኒስቴር እና የክልል ፍትሕ ቢሮዎች የጋራ ጉባኤ በዛሬው ዕለት በሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በሀዋሳ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል፡፡

ጉባኤው በሲዳማ ክልል የአገር ሽማግሌዎች ምርቃት የተጀመረ ሲሆን ፣ የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር ክቡር አቶ ደስታ ሊዳሞ በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው ፍትሕ ለአንድ ሀገር የጀርባ አጥንት በመሆኑ ሁላችንም ለፍትሕ ትራንስፎርሜሽን መሳካት በጋራ መረባረብ አለብን ብለዋል፡፡

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፍትሕና የሕግ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ክብርት ወይዘሮ እፀገነት መንግስቱ በጉባኤው ተገኝተው የፍትሕ ሪፎርም ለአገራችን አንዱና ዋናው መሆኑን አንስተው ዘርፉ የህዝባችንን ጥያቄ መሠረት በማድረግ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አማካኝነት ሰፊ ሀገራዊ ጥናት የተካሔደ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በዚህም ጥናት የተገኙ ጠንካራና መሻሻል የሚገባቸውን ጉዳዮች የሚመለከተው አካል በተገኘበት ውይይት መደረጉን አውስተው እንዲህ ዓይነት ውይይቶች ለፍትሕ ዘርፉ መጠናከር ትልቅ አስተዋፆኦ ስላላቸው ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አውስተዋል፡፡

በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ተስፋዬ ዳባ በመድረክ መክፈቻ ንግግራቸው ወቅት እንደገለጹት የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ቅንጅታዊ አሠራር ወሳኝ መሆኑን አውስተው ፍትሕ ሚኒስቴር የ2016 የ6ወር በጀት ዓመት የአፈፃፀም ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበበት ወቅት በአገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ የክልል ፍትሕ ቢሮዎች አፈፃፀም የቀረበበት መሆኑ የዚህ የጋራ ጉባኤ ውጤት በመሆኑ ይህ የጋራ ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረው ለመድረኩ መሳካት ድጋፍ ያደረጉትን እና የተባበሩትን የሲዳማ ክልል ፍትሕ ቢሮ፣ የአውሮፓ ህብረት (European Union) እና የተበባበሩት መንግስታት የወንጀል እና አደንዛዥ እፅ ጽ/ቤት (UNODC) አመስግነዋል፡፡

በመድረኩ የ2016 በጀት ዓመት የተጠቃለለ አገራዊ የፍትሕ ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት በፍትሕ ሚኒስቴር የስትራቴጂክ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በአቶ ደሳለኝ መንግስቴ አማካኝነት ቀርቦ በፍትሕ ሚኒስቴር የተቋም ግንባታና ሪፎርም ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ኤርሚያስ የማነብርሃን አወያይነት የቀረበውን ሪፖርት አስመልክቶ ከመድረክ አስተያየት እና ጥያቄዎች ተነስተው ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡

ጉባኤው ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት የሚካሔድ ሲሆን በጉባዔው የፍትሕ ሚኒስቴር እና የክልል ፍትሕ ቢሮዎች ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች እንዲሁም የፌደራል መንግሥት ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች በተጋባዥነት ተገኝተዋል፡፡

Tagged Under: Access to Justice appropriation Budget bureaus city Civil Society Community Justice conference Economic European Union finance fiscal hawassa hawassa city judicial reform Justice Justice Ministry Justice Reform ministry national justice plan Performance Report Regional Regional Justice Bureaus Rule of Law sidamo sidamo region spending stakeholders UNODC
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች