በተጠናቀቀዉ የ2015 የበጀት ዓመት በሀገር አቀፍ ደረጃ በድምሩ 17,048 መዛግብት ለድርድር የቀረቡ ሲሆን ከእነዚህም ዉስጥ 5,274 በስኬት ሲጠናቀቁ ቀሪዎቹ 11,774 በሂደት ላይ መሆናቸዉን በክልሎች የጋራ ጉባኤ በቀረበዉ ሪፖርት ላይ ተገልጧል፡፡ በዚህም ምክንያት የፍርድ ቤት ጫናን በመቀነስ ጊዜ እና ወጪን በመቀነስ አለመግባባትን የመፍታት ባህል እያደገ መምጣቱን ያሳያል።
ሪፖርቱን ያቀረቡት በፍትሕ ሚኒስቴር የስትራቴጅክ ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ደሳለኝ መንግስቴ በተያያዘም የግልግል ዳኝነት ጉዳዮች በተመለከተም ክትትል የተደረገባቸዉ 10 መዛግብት አጠቃላይ የገንዘብ መጠናቸው ከ887,602,177.64 ዶላር እና 7,800,000 ዩሮ በላይ ሲሆን ከነዚህም ዉስጥ ዉሳኔ ካገኘ መዝገብ 7,571,340.00 ዩሮ ያለአግባብ የቀረበ ክስ ተከላክሎ ማስቀረት ተችሏል ብለዋል፡፡
እንደ አገር በበጀት አመቱ በዐቃቢያነ ሕግ እጅ ከነበሩ 198,439 የምርመራ መዝገቦች መካከልም 188,875 መዝገቦች ላይ ዐቃቤ ሕግ የተለያዩ ውሳኔዎችን የሰጠ ሲሆን 172,940 የክስ መዝገቦች በክርክር ተደርጎባቸዋል፡፡
ከሙስና ወንጀል ጉዳዮች ጋር ከመሬት፣ ካሳ ክፍያና የመንግሥት ቤት ጋር በተያያዘ የተፈፀሙ ህገወጥ ድርጊቶችን መመርመርና መክሰስ በተመለከተ ከ1,397,000,000 ብር በላይ ፣ ከ 13, 442 ካሜ በላይ ቦታ እንዲሁም 4 መኖሪያ ቤቶችን እና 11 የኮንደሚኒየም ቤቶችን በመዘበሩ ከ 274 በላይ ግለሰቦች ላይ ክስ መመስረቱም ተገልጧል፡፡
በኢኮኖሚ ላይ የተፈፀሙ ህገወጥ ድርጊቶችን በተመለከተ በተለያዩ መዝገቦች 11 ተከሳሾች መንግሥት ላይ ቀረጥና ታክስ ብር 48, 862,616.34 ጉዳት እንዲደርስ ያደረጉ ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ መመስረቱንና ፍትሕና ፀጥታ ዘርፍ በሥልጣን አለአግባብ መገልገል ላይ የተፈፀሙ ህገወጥ ድርጊቶችን መመርመርና መክሰስ ስልጣናቸዉን አለአግባብ በመገልገል ከ231,530,000 ብር በላይ ለግል ጥቅማቸው ባዋሉና እና የተለያዩ የሙስና ወንጀል በፈፀሙ ከ 30 በላይ የፌደራል ፖሊስ አባላት፣ዳኛ፣ዐቃቤ ሕግ፣ ጠበቃ ፣የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት፣የፋይናንስ ኢንተለጀንስ ሃላፊ፣ የኢንሳ ሠራተኛና ግብረ አበሮቻቸው ምርመራ ተጠናቆ ክስ ተመስርቷል፡፡
በሴቶችና ሕፃናት የሚፈጸሙ ልዩ ልዩ ወንጀሎች አፈጻጸም ውጤታማነት ከማሳደግ አንፃር በሀገር አቀፍ ደረጃ 4,297 መዛግብት ርመራቸው ተጠናቆ ለዐ/ሕግ የደረሱ ሲሆኑ ከእነዚህ መካከል 4195 መዝገቦች ላይ ዐቃቤ ሕግ የተለያዩ ውሳኔዎችን መስጠት ተችሏል ፡፡
ከሕግ ማርቀቅ እና ማረም ስራ ጋር በተያያዘ በድምሩ 216 ህጎችን ማርቀቅ መቻሉ የተገለፀ ሲሆን 184 ጉዳዮች ቀርበው በሁሉም ጉዳዮች ላይ ተገቢው እርማት መደረጉም በሪፖርቱ ተገልጧል፡፡
በጥቅሉ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚቀርበዉ አገር አቀፍ የፍትሕ ሪፖርት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የተገለፀ የተሻለ የተዋረድና የጎንዮሽ ቅንጅታዊ አሠራርን ለማጎልበትም ከፌደራል ፍትሕ አካላት ጋር በአዲስ አስተሳሰብ ቅንጅታዊ ስራዎች መጀመሩንና ከክልሎች ጋር በቋሚነት የጋራ መድረኮች እየተደረጉ ሀገራዊ ሪፖርት እየቀረበ የአፈፃፀም ግምገማ እየተደረገ ነዉ፡፡
ወደፊት ይህንን ተግባር አጠናክሮ ለማስቀጠልም በፍትሕ ሚኒስቴር በኩል እየተደረገ ያለዉን ክትትልና አገዛ በቀጣይ በጀት ዓመት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በመድረኩ ተገልጧል፡፡
ሪፖርቱን መሠረት ያደረገ ውይይት የተደረገ ሲሆን ውይይቱን የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ፍቃዱ ጸጋ እና የተቋም ግንባታ እና ሪፎርም ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ኤርሚያስ የማነ ብርሀን መርተውታል፤ ከተሳታፊዎች ለተነሱም ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል።